የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር የተለያዩ የስእል ሥራዎችን ለብሄራዊ ሙዚየም አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር የተለያዩ የስእል ሥራዎችን ለብሄራዊ ሙዚየም አበረከተ
ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር የሰዓሊ ግርማ ህይወትን ጨምሮ በተለያዩ ሰዓሊያን የተሰሩ ስእሎችን ለብሄራዊ ሙዚየም አበረከተ። የሰዓሊ ብርቱካን ደጀኔ፣ አብዱልቃድር መሃመድ፣ ብሩክ ማሞና ጌድዮን ማርቆስ የስዕል ስራዎችም በሙዚየሙ በቅርስነት እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ሰዓሊ ግርማ ህይወት በትውልድ ኢትዮጵያዊ፤ በዜግነት ደግሞ ስዊድናዊ የነበሩት አንጋፋ የጥበብ ሰው ናቸው። ሙዚየሙ የተረከበው የሰዓሊ ግርማ ሥራ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድርና የአድዋ ውጊያ ውሎ የጀግንነት ታሪክ የሚያሳይ የቆየ የጥበብ ውጤት ነው ተብሏል። የሙዚየሙ የስነ-ጥበብ ተመራማሪ አቶ ግርማ ቡልቲ የስዕል ስራዎቹ ትውልድን ለማስተማርና ለምርምር ስራ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል። በመሆኑም ስእሎቹ በሙዚየሙ መቀመጣቸው ተገቢው እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው እንዲቆዩ፤ የአገሪቱን ባህልና ታሪክም ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል። አቶ ግርማ ቡልቲ አክለውም የጥበብ ባለሙያዎችን በማበረታታት ለአገራቸው ሰላምና አብሮነት እንዲሰሩ ማድረግ፤ ትውልዱ አዳዲስ ስራዎችን በመፍጠር የእራሱን አሻራ እንዲያኖር ማበረታታት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል። በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙት ሃላፊ አቶ ፈንታ በየነ በበኩላቸው የጥበብ ባለሙያዎቹ ለአገራቸውና ለህዝባቸው በመቆርቆር ያከናወኑትን በጎ ተግባር አድንቀዋል። የስዕል ስራዎቹ ሰላምንና ፍቅርን የሚያስተምሩ በመሆናቸው የያዟቸውን መልዕክት ለትውልድ ለማስተላለፍ በብሄራዊ ሙዚየሙ መቀመጣቸው ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አክለዋል። የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራጺያን ማህበር ፀሃፊ አቶ ወንድወሰን ከበደ የጥበብ ውጤቶቹ ወደ አገር ቤት መምጣታቸው በአውሮፓና በሌሎች አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያን የጥበብ ስራዎችን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል። ቅርሶቹ እንክብካቤና ጥበቃ ተደርጎላቸው ዘመን ተሻጋሪ ሆነው ትውልድን እንዲስተምሩ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ የማህበሩ አባላት መልክታቸውን አስተላልፈዋል። የሰዓሊ ብርቱካን ደጀኔ፣ አብዱልቃድር መሃመድ፣ ብሩክ ማሞና ጌድዮን ማርቆስ የስዕል ስራዎችም በሙዚየሙ በቅርስነት እንዲቀመጡ ተደርገዋል።