የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዜናን በማሰራጨት ተግባር ብቻ መወሰን የለበትም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዜናን በማሰራጨት ተግባር ብቻ መወሰን የለበትም
ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን እያጠናቀረ ከሚያሰራጨው ዜና ባሻገር በሌሎች የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ላይም መሰማራት እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ተናገሩ። ኢዜአ ከአዲስ አበባ ባሻገር በመላው አገሪቱ ባሉት ከ37 በላይ ቅርንጫፍ ቢሮዎቹና ወኪሎቹ አማካኝነት ዜናዎችን እያጠናቀረ በምስልና ድምፅ አስደግፎ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በኩል የሚያሰራጭ አገር አቀፍ የሚዲያ ተቋም ነው። ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ሚዛናዊ፣ ተደራሽና ሰፊ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ምክክር ጀምሯል። በዚሁ መድረክ ላይ ''የዜና አገልግሎቶች ዓለማቀፍ ተሞክሮ'' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ናቸው። ኢዜአ ሚዛናዊ መረጃን በማጠናቀር ማሰራጨት ተግባር ላይ ብቻ መወሰን እንደሌለበት ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ የተናገሩት። ተቋሙ ሰፊ የሆነ የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ የተግባቦት ስራዎች ላይም ማተኮር እንዳለበት በመጥቀስ። ኢዜአ ዜና ከማጠናቀር ባለፈ ሌሎች መረጃዎችን ለሚፈልጉ አካላት በሚፈልጉት መልክ አደራጅቶ ማቅረብ እንዳለበት ነው የዩኒቨርስቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ ያስገነዘቡት። ከዚህ አኳያ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ማካሄድ፣ የግልና የመንግስተ ተቋማትን ግንኙነትን በማሳለጥ የፕሬስ ሁነቶችን ማዘጋጀት፣ የሚዲያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ማዘጋጀትና ለሚዲያ ማቅረብ ተቋሙ በተጨማሪነት ሊያከናውናቸው የሚችላቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ስምምነት በመፍጠር ፋይናንስ ነክ የዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በማዘጋጀት ማሰራጨትንም አክለዋል። እንደዚሁም ኢዜአ እንደ መፅሄት ያሉ የህትመት ውጤቶችንና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን በመስጠት የውስጥ ገቢውን ማሳደግ እንደሚችልም ገልፀዋል። ገቢውን ከማሳደግ ጎን ለጎን የመረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚቻልም አብራርተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጫኔ ሽመካ እንዳሉት የአገሪቱ ዋና የዜና ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው ኢዜአ በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል። ህዝቡ ነፃና ተአማኒ መረጃ እንዲያገኝ ከባድ ኃላፊነት የተጣለበት ይህ ተቋም በቀጣይም የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።