አንድነት በማጠናከር ሰላምን በአስተማማኝነት መጠበቅ ይገባል--- ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
አንድነት በማጠናከር ሰላምን በአስተማማኝነት መጠበቅ ይገባል--- ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ማትያስ
ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 የሀገሪቱ ዜጎች ለዘመናት ያዳበሩትን አንድነት በማጠናከር ሰላምን በአስተማማኝነት መጠበቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ሊቀጳጳስ ብፁኡ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።
ፓትሪያሪኩ ዓመታዊውን የቁሉቢ ገብርኤል ክብረ- በዓል ለማክበር ትላንት ማምሻውን ድሬዳዋ በገቡበት ወቅት የአስተዳደሩ አመራሮችና የእምነቱ ተከታዮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቡነ ማትያስ በድሬዳዋ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ተወግዶ ሰላም መስፈኑ አስደሳችና መጠናከር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ይህን ሃብት የሁሉም ቤተ-እምነት ተከታዮች ተባብረው በአንድነት በመጠበቅ የጥቂት ሰላም አደፍራሾች እንቅስቃሴን በጋራ መከላከል እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
"የድሬዳዋ መገለጫም አንድነት፣ ፍቅር ፣ ሰላም መከባበርና መዋደድ ነው፤ ጥፋትና ጥል የድሬዳዋ መገለጫ አይደለም "ብለዋል፡፡
አንዱ የሌላውን እምነት ተከታይ ማክበር ፣ ማፍቀርና መርዳት በህብረት ለመጽናትና ለመቆም መሠረታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ለሁሉም ቤተ-እምነቶች ለሰጠው የይዞታ ማረጋገጫ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
"ይህ ተግባር የድሬዳዋን ህብረት፣ ፍቅርና አንድነት የሚያጠናክር ነው" ብለዋል፡፡
ቤተ-ክርስቲያኗ ለድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ያዘጋጀችውን የባህላዊ አልባሳትና ስጦታም አስረክበዋል፡፡
በቅርቡ በምሥራቅ ሐረርጌ አንዳንድ ከተሞች በተፈጠረው ችግር ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡት የተደረገውን የ250 ሺህ ብር ድጋፍና ከካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የተገኘውን 500 የፕላስቲክ ሸራ ለተጎጂ ቤተሰቦች ሰጥተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ ለተሰጣቸው ሽልማት አመስግነው በዓሉ የሰላምና የደስታ በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
በቤተ-እምነቶች ላይ የሚከናወነው ጥፋት የማንንም እምነት እንደማይወክል ተናግረዋል፡፡
"መስኪድን የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ ቤተ-ክርስቲያንን ደግሞ የእሰልምና አምነት ተከታዮች ሊጠብቁ ይገባል"ብለዋል፡፡
አንድ ጊዜ ብሔርን ሌላ ጊዜ ኃይማኖትን ተገን በማድረግ የህዝብ አንድነትና ፍቅር ለመከፋፈልና ሀገርን ለማናጋት የሚደረገው ጥረት በምንም መንገድ እንደማይሳካ አስታውቀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ሰሞኑን ለቤተ-እምነቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠቱን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።
የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተሰጣቸውም ለእስልምና ፣ ኦርቶዶክስ እና የፕሮቴስታንት ቤተ-እምነቶች ነው፡፡