ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የጸጥታና የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥታ ሰርታለች --- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢዜአ ታህሳስ 17 / 2012 ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በምስራቅ አፍሪካ የጸጥታና የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥታ መስራቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ)ሊቀ መንበርነት ስትሰራ ቆይታለች። በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሂደው 13ኛው የኢጋድ መሪዎች ጉባኤ ላይ የሊቀ መንበር ሃላፊነቷን ለሱዳን ማስረከቧም የሚታወስ ነው። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሁንም ኢትዮጵያ እንደኢጋድ አባል አገርነቷ ለተቋሙ ስራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች። አገሪቷ ላለፉት አስርት ዓመታት የኢጋድ ሊቀ መንበር ሆኗ በቆየችባቸው ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ ፈተና የነበሩት የሰላምና የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት ትኩረት አድርጋ መስራቷን ጠቁመዋል። በተለይ በደቡብ ሱዳን የነበሩትን የሰላምና የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት በርካታ ተግባራት ማከናወኗን ገልጸው፤ በሰላም ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓንና ተፋላሚ ወገኖች እንዲስማሙ ለማድረግ ስትጥር መቆየቷን አውስተዋል። ሶማሊያ መንግስት አልባ ሆና በግጭትና ጦርነት ችግር ውስጥ ገብታ መቆየቷን ያስታወሱት አቶ ነብያት፤ ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው ስራዎችም የአገሪቷ መንግስት ለመመረጥ የተቻለበትና የጸጥታ ሁኔታው የተፈጠረበት ጊዜ ላይ መደረሱን አመልክተዋል። እንደ አቶ ነብያት ገለጻ፤ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና ክልላዊ ትስስሮች ላይም የተሻለ እንቅስቃሴ ስታደር ቆይታለች። በኢትየጵያና ጅቡቲ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ትስስሮች መፍጠሩ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል። የተፈጥሮ አደጋ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የከባቢ አየር ለውጥ ስራዎች ላይም የኢጋድ አባል አገሮች በጋራ እንዲሰሩ መደረጉንም አክለዋል። የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እ.ኤ.አ በ1986 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከአባል አገራት አንዷ ሆና ቆይታለች። ኢጋድ ሲቋቋም ዋነኛ ትኩረቱ ድርቅና ድርቅን መቋቋምን ትኩረት የነበረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ከ1996 ጀምሮም የልማትና ክልላዊ ትስስር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም