ቀጥታ፡

ኤጀንሲው በጤና ተቋማት የቤተ ሙከራ ማሽኖች የሊዝ ግዥ አሰራር ስርዓት እየዘረጋሁ ነው አለ

ኢዜአ ታህሳስ 17/2012፡- የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በሀገሪቱ በሚገኙ ጤና ተቋማት የቤተ ሙከራ ማሽኖች የሊዝ ግዥ አሰራር ስርዓት እየዘረጋ መሆኑን አስታወቀ። በስርዓቱን አተገባበር ዙሪያ  ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመገምገም ያዘጋጀው የምክከር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ጊጋር በዚህ ወቅት በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ኤጀንሲው ካለፈው ዓመት ወዲህ በሀገሪቱ ለሚገኙ ህክምና ተቋማት የቤተ ሙከራ ማሽኖች ሊዝ ግዥ አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው። የሊዝ ሥርዓቱ ከሆስፒታል ጀምሮ በሁሉም ጤና ተቋማት ያለውን የቤተ ሙከራ አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ሳይቆራረጥ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በጤና ተቋማት ከሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንዱ የቤተሙከራ ግብአት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ህሙማን አገልግሎቱን ያለማግኘት እና ከመንግስት ጤና ተቋም ወደ ግል ጤና ተቋም መላላክ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ ከፍተኛ የታካሚ ቁጥር ባለባቸው ሆስፒታሎች የሚሰጠው አገልግሎት በሰዓቱ አለመድረስና ቀጠሮ መብዛት ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው  ይህንን  ለማቃለል ፕሮጀክት ተቀርፆ ስራ ውስጥ መገባቱን አመልክተዋል። የውጭ ሀገር አቅራቢዎች በነፃ የሚያስገቡትን የደም፣የስኳር፣የጉበትና የልብ መመርመሪያ ማሽኖችን በሊዝ በመከራየትና  ኤጀንሲው ለማሽኖቹ የሚሆን ግብዓት  በማቅረብ ህብረተሰቡ የምርመራ አገልግሎት ሳይቆራረጥ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። እንደ አቶ ጎይቶም  ገለጻ እስካሁን የሊዝ የጨረታ ሂደቱን ያሸነፉ ሰባት ዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ስራ ውስጥ ገብተዋል፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለ284 ከፍተኛ ሆስፒታሎችና ለ109 መለስተኛ ሆስፒታሎች የደም (ሔማቶሎጂ)፣ 5 ሺህ 200 የስኳር (ግሉኮሜትር)፣ እና የጉበትና የልብ (ኬሜስትሪ) መመርመሪያ ማሽኖች ቀርበዋል። እነዚህ ማሽኖችን በመትከል መጠቀም ከጀመሩና ከፍተኛ የተገልጋይ ቁጥር ካለባቸው ሆስፒታሎች መካከል ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ አይደር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ጅማ ባህርዳርና ደሴ ይገኙበታል። ማሽኖቹ ብልሽት ቢያጋጥማቸው አቅራቢ ካምፓኒው ጥገና ስለሚደረግላቸው ካሁን በፊት  ያጋጥም የነበረውን የአገልግሎት መቆራረጥ መከላከል ተችሏል። "በመጀመሪያው ምዕራፍ አዲስ አበባና በክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ ጤና ተቋማት  አዳርሰናል" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ሁሉንም የሀገሪቱ አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል። የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ሁንዴ  በበኩላቸው " በውሉ መሠረት ለማሽኖቹ የአገልግሎት ክፍያ ብቻ በመፈጸም ሆስፒታሉ ተጠቃሚ መሆኑ ካሁን በፊት ሲያስቸግረን የነበረውን የላብራቶሪ አገልግሎት መቆራረጥ በእጅጉ አስቀርቷል" ብለዋል። በተለይ የማሽኖቹ ባለቤት የሆኑት ካምፓኒዎች አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ለማሽኖቹ የሚሆን የቤተሙከራ  ግብዓት ፈጥነው ስለሚያቀርቡ ማህበረሰቡ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኗል።   በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ሁለት ዘመናዊ የቤተሙከራ ማሽኖች የሚታዘዙ አብዛኛውን ምርመራዎች የመሸፈን አቅም እንዳላቸው አቶ ተሾመ አብራርተዋል። "በሊዝ ማዕቀፉ ቀድመን ስራ ውስጥ ገብተናል"  ያሉት ደግሞ  የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የላብራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ብርሃነመስቀል ተገኔ ናቸው። በአገልግሎቱ ብዛት ያላቸው ሰዎች  ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልከተዋል። ሆስፒታሉ የተረከባቸው ሁለት ዘመናዊ ማሽኖች ከዚህ ቀደም አንድ ቀን አድሮ ይመጣ የነበረው የህሙማን  የቤተሙከራ  ናሙና ውጤት ወደ ሁለት ሰዓት ከማሳጠር ባለፈ ጥራቱ አስተማማኝ እንደሆነም አስረድተዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም