ቀጥታ፡

ኦነግ ለምርጫው ዝግጀት እያደረገ መሆኑን ገለጸ

ኢዜአ ታህሳስ 17 / 2012 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዘንድሮ ለሚካሔደው ብሔራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ካለችበት የለውጥ ሒደት ጋር ተያይዞ 'ይካሄድ ወይም አይካሄድ' በሚል የተለያዩ ሀሳቦች እየተስተናገዱ ይገኛል።

አገሪቷን እየመራ ያለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ወደ ብልጽግና ፓርቲነት ለመሸጋገር  ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ አውቅና ያገኘ ሲሆን ምርጫው በተያዘለት ጊዜም ይካሄድ ዘንድ ጠንካራ አቋሙን አሳውቋል።

ኦነግም እንደ ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው መካሄድ እንዳለበት ጽኑ እምነት እንዳለው ገልጿል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንደሚናገሩት፤ ድርጅታቸው በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነው።

''ኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በደርግም፣ በኢህአዴግ ዘመንም 'ለይስሙላ' እንጂ ትክክለኛ ምርጫ ተካሄዶ አያውቅም'' ብለዋል።

ፓርቲው ዘንድሮ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ተካሄዶ "ሕዝቡ ይወክለኛል" የሚለውን አካል እንዲመርጥ የበኩሉን ሚና ይወጣል።

ትክክለኛ ዴሞክራሲ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ግንባታ መሰረት፣ የሰላም ማምጫና ማረጋገጫ መሆኑን "በማመን 'ኦነግ' የድርሻውን ይወጣል" ብለዋል።

እስካሁንም ድርጅቱ የፓርቲውን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሰነድ ከምርጫ ቦርድ ተቀብሎ ለምርጫ የሚረዱ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው።

ፓርቲው በአገራዊ ፓርቲነት የተመዘገበ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቀጄላ፤ ''በኦሮሚያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቢሮዎችን ከፍቷል'' ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ፓርቲው ለምርጫው የሚያስፈልገውን ጥናት ማካሄድ ላይ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለምርጫ አስፈላጊ ነገሮችን እያሟላ መሆኑን ገልጸዋል።

የምረጡኝ ዘመቻ ሲጀመርም ፓርቲው በሚወዳደርበት አካባቢ ከምርጫ ጋር ተያያዥ የሆኑ ትምህርቶችን ለመስጠት ዕቅድ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ቀጄላ ገለጻ፤ የ'ኦነግ' ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ትክክለኛ የምርጫ ስርዓት እውን መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

ለዚህም ኦነግ ምንም እንኳን ለምርጫው አጭር ጊዜ የቀረ ቢሆንም 'በየትኛም መልኩ ምርጫው መተላለፍ የለበትም' ብሎ ያምናል ሲሉ ያረጋግጣሉ።

አቶ ቀጄላ 'ኦነግ'ን የተመለከተ የተወሰኑ አካላት የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸውን አውስተው፤ ድርጅቱ መልካም ስሙን ይዞ እንዲቀጥል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ወደ አገር ውስጥ እስኪገባ ድረስ ለሶስት አስርት ዓመታት በውጪ የቆየና በኢትዮጵያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት እስከ መፈረጅ የደረሰ ፓርቲ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም