ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ
ኢዜአ ታህሳስ 17 / 2012 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ። የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዛሬ ኢንጂነር አዜብ አስናቀን ጨምሮ 50 ሰዎች ላይ ክሱን የመሰረተው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ በተካሔደ የደን ምንጣሮ ስራ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ደኖችን የመመንጠር፣ የማጽዳትና በአካባቢው ወደ ተዘጋጀለት ቦታ የማጓጓዝ ስራ ለማከናወን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ሕዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም ከአምስት ብሊዮን ብር በላይ ውል ፈጽሟል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል በተደረገው ውል መሰረትም የምንጣሮ ስራው ውሉ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ በ720 ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበት ይደነግጋል። መስሪያ ቤቱም በውሉ መሰረት ያልተከናወኑ ሥራዎችን ቀደም ብሎ በመለየት በወቅቱ እርምጃ መውሰድ ይገባው ነበር።
የክስ መዝገቡ እንደሚያመለክተው ግን ኢንጂነር አዜብ አስናቀ የስራው 30 በመቶ ብቻ እንደተከናወነ እያወቁ ውሉ እንዲሻሻልና ጊዜው እንዲራዘም አድርገዋል።
መስሪያ ቤቱ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ባደረገው ውሉ መሰረት የመጀመሪያ ዙር ክፍያ የሚፈፀመው የስራውን 50 በመቶ ሲያከናውን ነው። ይህን ያህል ማከናወኑ ሲረጋገጥ ከአጠቃላይ ዋጋ 30 በመቶ ለኮርፖሬሽኑ ይከፈላል።
የክስ መዝገቡ እንደሚያመለክተው፤ ኢንጅነር አዜብ ከቀድሞው ውል ላይ ከተጠቀሰው መጠን 20 በመቶ በመቀነስ 'ስራው 30 በመቶ ሲከናወን የመጀመሪያ ዙር ክፍያ 30 በመቶ ይፈፀማል' በሚል እንዲሻሻል አድርገዋል።
በመሆኑም የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር ከአጠቃላይ ክፍያው 20 በመቶ (ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ) አላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
ኢንጂነር አዜብ አስናቀና በዚህ መዝገብ 3ተኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ብረዳ ሃይሉ በውሉ መሰረት ስራው መጠናቀቅ በሚገባው ወቅትና ጊዜ መጠናቀቁን በማረጋገጥና ያልተከናወነውን ሥራ በመለየት እርምጃ መውሰድ ሲጋባቸው ይህን አላደረጉም።
እንደውም መስሪያ ቤቱን በሚጎዳ መልኩ ውሉ እንዲሻሻል በማድረግ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሳቸው ክሱ እንደተመሰረተባቸው ሰነዱ ያትታል።
ኢንጂነር አዜብ (በመዝገቡ 2ተኛ ተከሳሽ)ና 4ተኛ ተከሳሽ አቶ አብይ ይሁን የተሰኙ ተከሳሽ የስራ ውል ስምምነት ሳይፈፀም 500 ሚሊዮን ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈፀም በማድረግ ከፍተኛ መጠን ያለው የመንግስት ገንዘብ እንዲባክንና ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮርፖሬት ኒው ቢዚነስ ዲቬሎፕ ኃላፊ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል አንደኛ ተካሳሽ ናቸው።