የኢትዮያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ኢዜአ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓም የኢትዮያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ። ምርት ገበያው ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽንና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር በቆሎ ወደ መጋዘን ለሚያስገባ ማንኛውም አባል ወይም ደንበኛ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል። የኢትዮያ ምርት ገበያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አገልግሎቱ አንድ አምራች ወይም ተገበያይ በኢትዮጰያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባትና ደረሰኙን እንደ ማስያዥ በመጠቀም ከምርት ገበያው ጋር በጣምራ ከሚሰሩ ባንኮች የብድር አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር ነው። በዚህም አርሶ አደሮችን ያቀፈ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖች፣ የግብርና ምርት አቀነባባሪ ድርጅቶችና አቅራቢዎች የአጭር ጊዜ ብድር የሚያገኙበትን የመጋዘን ብድር አገልግሎት በቡሬና ነቀምት ቅርንጫፎች ለመጀመር መዘጋጀቱንም ጠቁሟል። በአገልግሎቱም ከዚህ በፊት ምርቱ ለግብይት እንደደረሰ መሸጥ ግዴታ ውስጥ ይገባ የነበረውን አርሶ አደር ጥሩ ዋጋ ሲያገኝ በመጋዘን ያስቀመጠውን ምርት በምርት ገበያው በኩል በመሸጥ ብድሩን መክፈል እንደሚያስችለውም ተገልጿል። የመጋዘን ብድር አገልግሎት የሚያገኙ ተበዳሪዎች መያዣ እንዲሆን ካስገቡት ምርት ውጪ ሌላ ንብረት ለመያዣነት የማያስፈልጋቸው ሲሆን የራሳቸው የሆነ የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲኖራቸው አይጠበቅባቸውም። አሰራሩ ለባንኮች አዲስ የብድር አገልግሎት ከመፍጠሩም ባሻገር በምርት ገበያና በባንኮች መካከል ምንም አይነት የሰነድ ልውውጥ ሳይካሄድ ሁሉም ሂደት በኤሌክትሮኒክስ የቀጥታ ግንኙነት የሚፈጸም መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም ገበሬዎች፣ ህብረት ስራ ማህበራት፣ አቅራቢ ነጋዴዎች፣ የግብርና ግብአት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችና ገዢ ነጋዴዎች የመጋዘን ደረሰኙን በመጠቀም የስራ ማስኬጃና ማስፋፊያ ገንዘብ የሚሆን የአጭር ጊዜ ብድር ያገኛሉም ተብሏል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአገልግሎቱ ስምንት በመቶ የወለድ መጠን የሚያስከፍል ሲሆን ለአንድ ተበዳሪ ብድሩን ተመላሽ የሚያደርግበት ቀን ገደብ ለሻጭ ወይም ለአቅራቢ ሶስት ወር ሲሆን ለግዢ ደግሞ ሁለት ወር እንደሚሆንም የምርት ገበያው መግለጫ አመልክቷል።