ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ ነው---የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ ነው---የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ
ኢዜአ ታህሳስ 17 / 2012 ዓም ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ ና ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ከአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ጋር በመተባበር በምርትና አገልግሎት ጥራት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በባህርዳር አካሂዷል። የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት በሀገሪቱ የተረጋጋና ቀጣይነት ያለው ማይክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት ደረጃዎችን ተጠቅሞ ማምረትና አገልግሎት መስጠት ግዴታ ነው። "ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ ልኮ መሸጥ አይቻልም" ያሉት ዳይሬክተሩ አምራቾችና አገልግሎት ሰጭዎች ይህን አውቀው መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው እሰገንዝበዋል። ከውጭ በሚገቡትም ሆነ በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ መሸጥ ዋነኛ ችግር ሆኖ እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመዋል ። ደረጃ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ከችግሩ መውጣት እንደሚገባ አሳስበዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በማስወገድ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲዘልቁ ደረጃ አወጣጥን ከማሳደግ ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ። አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጭዎች፣ አስመጭና ላኪዎች እርስ በእርስ ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ በመስራት በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤጀንሲው በግለሰቦች ቤት ተመርተው ህዝብ የሚጠቀማቸውን እንደ ቆሎ፣ ጠጅ፣ አረቄና ለሌሎች ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ደረጃ ለማውጣት እየሰራ ነው። የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በበኩላቸው የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ጤናና ደህንነት ለማስጠበቅ ደረጃው የተረጋገጠ ምርት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በተዋረድ ስለደረጃ ያለውን የግንዛቤ ማነስ ለመፍታት ኤጀንሲው ቅንጅታዊ አሰራር ፈጥሮ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል ። ጥራት ያለው ምርት በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ተወዳዳሪነትንና ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። "ኤጀንሲው የደረጃ ሰርተፍኬት ከሰጠ በኋላ ተከታትሎ የመቆጣጠር ተግባር እያከናወነ አይደለም" ያሉት ደግሞ የቾይዝ ውሃ ፋብሪካ የምርት ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ስንታየሁ ናቸው። ኤጀንሲው በዘርፉ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በምክክር መድረኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።