ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልከቶ በሚካሄዱት ድርድሮች ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም እያራመደች ጥቅሟን እያስጠበቀች ነው ተባለ

ኢዜአ ታህሳስ 17/2012 የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልከቶ ከግብጽና ሱዳን ጋር በሚካሄዱት ድርድሮች ኢትዮጵያ ጠንካራ አቋም እያራመደች በመሆኑ ድርድሩ ጥቅሟን በአግባቡ የሚያስጠብቅ መንገድ እየተካሄደ ነው ሲሉ የተደራዳሪው ቡድን አባል ገለፁ።

ከሳምንት በፊት ካርቱም በተካሄደው ድርድርም ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የግድቡን የውሃ አሞላል ስሌት ግብጽና ሱዳን ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውም ተጠቁሟል።

ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የተወጣጡት የሳይንቲስቶችና ባለሙያዎች ሰብሳቢና ተደራዳሪ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንደተናገሩት፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር ኢትዮጵያ የሰየመቻቸው ተደራዳሪዎች በዘርፉ በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው።

ስለሆነም አገሪቱ የምታራምደው አቋም በአባይ ውሃ የመልማት መብትና ጥቅምን በሚያስጠብቅ መንገድ መሆኑንም ይናገራሉ።

ሱዳን ከዚህ በፊት ይዛው የነበረውን አቋም በማስቀየር ከኢትዮጵያ ጋር በአቋም እንድተባበር መደረጉን  ለአብነት በማንሳት።

ከዚህም በላይ ግብጽ በውሃ አሞላል ሂደቱና በግድቡ ግንባታ ላይ የነበራትን አቋም ማስቀየር መቻሉንም እንዲሁ።

ከሳምንት በፊት ካርቱም ላይ ተደርጎ በነበረው የሶስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም ከግድቡ የውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘቱንም ኢንጂኒየር ጌዲዮን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሀሳብ መሰረት የግድቡ ውሃ ከአራት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጊዜ እንዲሞላ ይደረጋል።

ኢትዮጵያ ያቀረበችው ይህ ሀሳብ በካርቱሙ ስብሰባ በሳይንቲስቶቹም ተቀባይነት ያገኘና እንደ መፍትሔ ሃሳብ የቀረበ እንደነበረም ነው ኢንጅነር ጌዲዮን የተናገሩት።

እስከ ካርቱሙ ስብሰባ ድረስ የግብጽ አቋም ኢትዮጵያ እና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የሌለበት በቀኝ ግዛት ወቅት የነበረው ስምምነት ይተግበር የሚለውን አቅምና ግድቡም ከተሞላ 12 ዓመት እና ከዚያ በላይ ጊዜ ይኑረው የሚል እንደነበር አስታውሰዋል።

በሚካሄደው ድርድር ግብጽ ወደ ኢትዮጵያ አቋም እንድትመጣ መደረጉ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።

በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ሳምንታት በኢትዮጵያ በሚደረገው የሦስቱ ሀገራት ስብሰባ ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ስምምነት ለመድረስ ድርድር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የውሃ አሞላል ሂደቱን በተመለከተ ግብጽ ያቀረበችውን ሃሳብ ተቀበለች፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ግፊት እየተደረገባት ነው የሚሉ አሉባልታዎች ከእውነት የራቁና ተደራዳሪዎቹን ጠይቆ ያላረጋገጠ ዘገባ ነው ሲሉ ኢንጂነር ጌዲዮን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንን ወቅሰዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ ከአሉባልታ ይልቅ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ጎን እንዲቆሙና ተደራዳሪዎቹን እንዲያበረታቱ ጠይቀዋል።

ለሚዛናዊ ዘገባም ተደራደራዳሪዎችን በመጠየቅ ትክክለኛውን መረጃ ለሕብረተሰቡ እንዲያቀርቡም መክረዋል።

የአሜሪካና የዓለም ባንክ ተወካዮች በድርድሩ ሂደት ከመታዘብ ያለፈ ምንም ዓይነት ሚና እንደሌላቸው ኢንጅነሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም