ቀጥታ፡

ስካይ ላይት ሆቴል በአፍሪካ ግዝፉ ሆቴል እንዲሆን እየሰራሁ ነው - የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢዜአ፤ ታህሳስ 17/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይ ላይት ሆቴል በአፍሪካ ግዝፉ ሆቴል እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

በአዲስ አበባ ከአመት በፊት ስራ የጀመረው የስካይ ላይት ሆቴል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤትነት የሚተዳደር ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በ345 አልጋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

አየር መንገዱ የሆቴሉን መኝታ ክፍል ወደ አንድ ሺህ በማሳደግ በአፍሪካ ግዙፍ ሆቴል ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ማስታወቁን ቮዬጅ አፍሪካ የተባለ ድረ ገጽ ዘግቧል።

ከአንድ አመት በፊት 345 መኝታ ክፍል በመያዝ ወደ ስራ የገባው ሆቴል በሁለተኛ ዙር የማስፋፊያ ግንባታ 640 መኝታ ክፍል ለመጨመር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና የንግድ ክፍል ኦፊሰር አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም "ግንባታው ከስብሰባ፣ ጉባኤና ከኹነት ዝግጅቶች የሚገኘውን ተጨማሪ ገቢና ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የቅንጦት ተጓዥችን መሰረት በማድረግ የሚከናወን ነው" ማለታቸውን ድረ ገጹ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት እ.ኤ.አ በ2025 በአፍሪካ ቀዳሚ የአቪየሽን ግሩፕ ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ለዚህም ይረዳው ዘንድ የ15 ዓመት ስትራቴጂያዊ ፍኖተ ካርታ ነድፎ እየሰራ ነው።

አየር መንገዱ ሰባት የትርፍ  ማዕከሎችን በመንደፍ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህም በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ ዓመታዊ ትርፉን አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ማቀዱን ሃላፊው ተናግረዋል።

የስካይ ላይት ሆቴል አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን የመኝታ ክፍሎቹ የከተማዋን ድንቅ አቀማመጥ እንዲያሳዩ ተደርገው መታነጻቸው ተጠቅሷል።

ሆቴሉ በተጨማሪ ሶስት ቅንጡ ሬስቶራንቶችን፣ ሙሉ ቀን አገልግሎት የሚሰጡ ምግብ ቤቶች፣ በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ የሆነ የቻይና ሬስቶራንት፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብ ቤትና ባሮችን ይዟል።

ሆቴሉ ሁለት ሺህ እንግዶችን መያዝ የሚችል ቦል ሩም ያለው ሲሆን አስፈላጊ ሲሆን አዳራሹን አምስት ቦታ በመክፈል በአንድ ጊዜ ከ 500 እስከ 800 ሰው ማስተናገድ ይችላል።

ግለሰቦች የሚያደርጓቸውን ዝግ ስብሰባ ለማስተናገድ የሚችሉ ሶስት አነስተኛ አዳራሾችና ተቋማዊ ውይይት የሚደረግባቸው ሁለት የግል የስብሰባ ክፍሎች አሉት።

ሆቴሉ ከቤት ውጭ የተሰራ የመዋኛ ገንዳ፣ አነስተኛ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳ፣ ስፓ፣ ጂምናዚየምና የጤና ማዕከል አለው።

የንግድ ክፍል ሃላፊው ኢሳያስ ወልደማርያም ጨምረው እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ በሶስተኛው የግንባታ ፕሮጀክት በአገሪቱ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻዎች ሎጆችን የመገንባት እቅድ አለው።

''ይህም የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ የራሱ የሆነ ከፍተኛ ሚና አለው" ብለዋል።

በሶስተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት በአገሪቱ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መገኛ ቦታዎች ላይ ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ሎጆችንና አነስተኛ ሆቴሎችን እንደሚገነባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም