የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሶስት ወራት ቆይታ ስራዎች

326
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው ስብሰባ መጋቢት 19 ቀን 2010  ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር ሆነው  ተመርጠዋል። መጋቢት 24 ቀን 2010  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር አብይ አሕመድን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። ዶክተር አብይ አህመድም ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ርክክብ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ዶክተር አብይ ቃለ መሀላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ የተደረገው የስልጣን ሽግግር ኢትዮጵያ ዘላቂ፣ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የህገ መንግስት ስርአት እንዳላት  የሚያሳይ ነው። ''ከጊዜው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና ለህዝብ ፍላጎት የሚገዛ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ስርአት እንደተገነባ የሚያመላክት ነው'' ብለዋል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር። "ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለመጀመር ያገኘቻቸውን እድሎች በወጉ አልተጠቀመችባቸውም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው የስልጣን ሽግግር በፖለቲካው መስክ አዲስ ምዕራፍ መጀመር የሚያስችል እንደሆነም አንስተዋል። ኢትዮጵያን ዓለም በአንድ በኩል በአግራሞት፣ በጥሞና እና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ አገራዊ ለውጥ ላይ እንደምትገኝ አመላክተዋል። መንግስት ያሳካቸው ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መፍታት የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶችም መኖራቸውን እንደሚያምንና እነዚህንም ችግሮች በማረም የተሻለ አገር ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል። አገሪቱን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ለማሸጋገርና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበት ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄድ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቅሰዋል። "አሁን ያለንበት ወቅት ከስህተቶቻችን ተምረን አገራችን የምንክስበት ወቅት ነው" ሲሉ ዶክተር አቢይ ተናግረዋል። "ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች ከፖለቲካዊ አመለካከት በላይ አንድነት ይበልጣል አንድነት የማያሸንፈው ችግር የለም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ለአገሩ አንድነትና ሰላም መስራት ይጠበቅበታል'' ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ በአገራዊ፣ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል። በአገር ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ ፈጥረው ህዝብን አዳምጠዋል። በውይይታቸውም ከህብረረተሰቡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ዘርፎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት መንግስት ህብረተሰቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት አገሮች ያደረጉት የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር ሚናዋን ለማሳየት ታሳቢ ያደረገ እንደሆነበር ተመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጂቡቲ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኬንያ ያደረጉት ጉብኝት ውጤታማና የአገሮቹን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል። ከአገሮቹ ጋር በተደረጉ ውይይቶችም በወደብ አጠቃቀም፣  በዜጎች ደህንነት፣  በመሰረተ ልማት ትስስርና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ ላይ በመወያየት በርካታ ስምምነቶች ተደርገዋል። የአገሮቹን የመንግሥታትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስሰሩን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ምክክር ለማድረግ ችለዋል። የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የገባው ቃል ተጠቃሽ ነው። በአገሮቹ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያደረጉት ስምምነትና የተወሰዱ እርምጃዎችም የጉብኝቱ ጠቀሜታ እንደሆነም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞችም የማስፈታት ተግባር አከናውነዋል። በዚሁ መሰረት እስረኞች ከሱዳን፣ ከግብጽ፣ ከኬንያና ሳዑዲ አረቢያ ተፈተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በግብጽ በእስር ላይ ይገኙ ኢትዮጵያውያንን አስፈትተው ይዘው በመመለስ ለዜጎች ያላቸውን የላቀ ክብር አሳይተዋል። በተጨማሪም በተለያዩ ጥፋቶች ተከሰው የተፈረደባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ 118 ኢትዮጵያውያን ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱም ተነግሯል። ኢትዮጵያውያኑ የሚፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለአገሪቱ መንግስት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እንደሆነም ይታወቃል። በግብፅ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል። በሊቢያ በስደት እያሉ በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን አጽም ከተቀበረበት በማምጣት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የመጨረሻ እረፍት እንዲያገኝ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱም ይታወቃል። በውይይቱ ወቅት ትኩረት ሰጥተው ካነሱት ሃሳብ መካከል የዜጎች ከእስር መለቀቅና በአሸባሪዎች በግፍ የተገደሉት አጽማቸው በአገራቸው በክብር እንዲያርፍ የማድረግ ጉዳይ ነው። ሁለቱን መሪዎች ባደረጉት ውይይት በሊቢያ በስደት የነበሩና በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች አጽማቸው ከተቀበረበት ቦታ ይወጣል። አጽማቸው የመጨረሻ እረፍት ወደ ሚያገኝበት ኢትዮጵያ እንዲገባ ስምምነት ላይም ተደርሷል። በሳዑዲ አረቢያ በህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ለዓመታት የቆየው ኢትዮጵያዊው ታዳጊ መሀመድ አብዱላዚዝ 21 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፈለው መደረጉም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለሳዑዲ መንግስት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የካሳ ክፍያው ተፈጽሟል። ዶክተር አብይ ታዳጊ መሀመድ ያለበት ሆስፒታል በመገኘት መጎብኘታቸው ይታወሳል። ወደ አገሩ የተመለሰው ታዳጊ መሐመድ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግብጽ ጉብኝታቸው መልስ በሳዑዲ አረቢያ በህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ለዓመታት የቆየው ታዳጊ መሐመድ አብዱልአዚዝና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ጥቃት ደርሶበት ህክምና ላይ የሚገኘውን ህፃን ብርሀኑ (አበጥር) ወርቁ ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በመገኘት ጎብኝተዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ ያደረገ ሰልፍ ዛሬ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቷ ከተሞች ተካሂዷል። በ1980ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ፓርቲን እንደተቀላቀሉ የሚነገርላቸው ዶክተር አብይ በስራ ህይወታቸው በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ከወታደርነት እስከ ሌተናንት ኮለኔል ማዕረግ ድረስ አገራቸውን አገልግለዋል። በተጨማሪም ብሄራዊ የመረጃና መረብ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ካገለገሉ በኋላ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የካቢኔ አወቃቀር ወስጥ የሳይንስ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል። የኦህዴድ እና ኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው እስከተመረጡበት ጊዜ ድረስም በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የቤቶችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነት ላይ እያገለገሉ ነበር። በትምህርት ዝግጅታቸውም በሰላምና ደህንነት፣ በቢዝነስ አስተዳድርና በኮምፒውተር ሳይንስ መስኮች ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ወይም ዶክትሬት ዲግሪ የደረሱ በሳል ፖለቲከኛ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም