ለኤርትራ ኤምባሲ ፅህፈት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
ለኤርትራ ኤምባሲ ፅህፈት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 16/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአዲስ አበባ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ቋሚ ጽህፈት ቤት የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።
ለኤምባሲው ግንባታ የሚያስፈልገውን ቦታ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ያዘጋጀው የከተማ አስተዳደሩ ነው።
በመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሰት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እያካሄዱት ባለው ጉብኝት ከኤርትራ ጋር በርካታ የልማት ትስስሮችን ለመፍጠር የሚያስችሉ አቅሞች መኖሩን መገንዘባቸውን ገልፀዋል።
አክለውም "የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር ለሚያስችለው የኤርትራ ኤምባሲ ቋሚ ጽህፈት ቤት ግንባታ ቦታ እንደ ገና ስጦታ ስናበረክት በአክብሮትና በወዳጅነት ነው" ብለዋል።
አዲሱ የአውሮፓዊያን ዓመትም የኢትዮጵያና ኤርትራ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር በጋራ የሚሰራበት እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
“ኢኮኖሚያችንን ከልመና ወደ ብልጽግና እንድናሸጋግር አብረን እንድንሰራ በኢትዮጵያ በኩል ልባችን፣ አዕምሯችን፣ እጃችን ክፍት ነው" ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአገራቱ መካከል ሙሉ ሰላም፣ ልማት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጠር በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩንም በማከል።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ኤምባሲው የሚገነበባትን ቦታ የኢትዮጵያ መንግስት በመስጠቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር፣በጋራና በሙሉ አቅም ለመስራት ምንም የሚያግድ ነገር የለም ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፤ የተጀመሩትን ስራዎች በቁርጠኝነት ለማስቀጠል መንግስታቸው እንደሚተጋም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ያለበቂ ምክንያት በመራራቃቸው ሳቢያ ያጧቸውን እድሎች ለማካካስ በሚያስችል መልኩ በሙሉ አቅም በጋራ ለመስራት አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።
"መጀመሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ታናሽ ወንድሜ ዶክተር አብይ 2ቱን ቀናት በሰርፕራይዝ እየቀያየርክ ለሰጠሀኝ ክብር ምስጋናዬ ከልብ ነው፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ያለ ምክንያት ተራርቀን ቆይተን ይሄ አሁን የተፈጠረው እድል ከዚህ የበለጠ ደስታ ስለሌለ ያለፈውን ኪሳራ እንዲመለስ ለማስቻል በሙሉ አቅማችን በአንድነት ለመሰራት ያለን ፍላጎት በመተማማን በሚመጣው አመት እንጀምራለን፤ የሚያግደን ነገር የለም፤ መስመራችንን ሳንስት የምንቀጥል መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ።" በማለትም ነው የገለጹት።
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቆይታቸው የሁለቱ አገራት የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር እየመከሩ ይገኛሉ።
በዛሬው እለትም የተለያዩ የልማት አውታሮችን ጎብኝተዋል።