በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የትምህርት ስራን አደናቅፈዋል ባላቸው ተማሪዎች ላይ አሰተዳደራዊ እርምጃ ወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የትምህርት ስራን አደናቅፈዋል ባላቸው ተማሪዎች ላይ አሰተዳደራዊ እርምጃ ወሰደ
ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 ፡- ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን አደናቅፈዋል ባላቸው አስር ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። የዩኒቨርስቲው የወጭ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ሲኒየር ዳይሬክተር ዶከተር አሸናፊ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ተማሪዎቹ እርምጃው የተወሰደባቸው ሌሎች ተማሪዎች ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ የደህንነት ሰጋት በመፍጠራቸው ነው። የከፍተኛ ትምህርት ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ተማሪዎቹን እንደ ጥፋት ደረጃ ተሳትፏቸው በመለየት ከትምህርታቸው ሙሉ ለሙሉ ከማሰናበት ጀምሮ እስከ ሁለት አመት የማገድ እርምጃ እንደተወሰደባቸው አስታውቀዋል። ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የተስተጓገለውን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ተማሪዎቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል ። ከዩኒቨርሲቲው የቦርድ አመራር ፣ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከክልል፣ ከጽጥታ አካላት፣ ከተማሪዎችና ከመምህራን ተወካዮች በተውጣጣ ግበረ ኃይል ውይይት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል ። ወደፊትም በመማር ማስተማሩ ስራ ላይ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች ላይ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀጠል በቂ ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል።