ኢትዮጵያና ቻይና በኮንስትራክሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቻይና በኮንስትራክሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
ኢዜአ ታህሳስ 16/2012.. የኢትዮጵያ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በስፋት ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ። የኮንስትራክሽን ትብብር ስምምነቱን ትናንት በቤጂንግ የተፈረመው በቻይና ጉብኝት በማድረግ ላይ በሚገኙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሃመድና በቻይና መንግስት የኮንስትራክሽን ተቋማት መካከል ነው። በዚሁ ወቅት ሚኒስትሯ ኢንጂኒየር አይሻ ባደረጉት ንግግር "ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ የሚረዳትን የ10 አመት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ነው፤ ይህን እቅድ ለማሳካት ደግሞ የቻይና የግንባታ ተቋማት ቁልፍ ሚና አላቸው" ብለዋል። ኢትዮጵያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎቿ የመኖሪያ ቤት የያዘችውን ውጥን እውን ለማድረግ የቻይናን ድጋፍ ትሻለች ሲሉም ገልፀዋል። በኮንስትራክሽን ዘርፉ በመታገዝ ባለፉት 15 አመታት ጠንካራ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ የቻለችው ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣውን ከተሜነት የሚመጥንና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎትን የሚያሟላ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ሲል ቻይና ዶት ኦርግ ድረ-ገጽ ዘግቧል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በከተማዋ ያለውን 4 ሚሊዮን ነዋሪ የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከቻይና የግንባታ ተቋማት ጋር በመተባበር የመገንባት እቅድ መያዙን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። የመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ በ27 ሄክታር መሬት ላይ የሚከናወን ሲሆን የቻይናው ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ግንባታውን እንደሚያከናውነው ድረ-ገጹ አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይና ኩባንያ የዲዛይን ስራውንና የቅድመ ግንባታ መደላድሎችን ማጠናቀቃቸውን ድረ ገጹ ዘግቧል።