"መደመር" ለዓለም የሚጠቅም አዲስ እሳቤ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
"መደመር" ለዓለም የሚጠቅም አዲስ እሳቤ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ
ኢዜአ ታህሳስ 16/2012 "መደመር ከአፍሪካ አልፎ ለመላው ዓለም ሊጠቅም የሚችል አዲስ አስተሳስብን ይዞ ብቅ ያለ እሳቤ ነው" ሲሉ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ፡፡ የመደመር እሳቤ የሚከተለው መርህ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር ለሚኖራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል። አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የመደመር እሳቤ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሊጠቅም የሚችል አዲስ እሳቤ ነው። አለም አቀፍ ግንኙነትን ለማጠናከር እና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ለማሳለጥ በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የተጀመረው የመደመር እሳቤ ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል። አምባሳደር ተሾመ፤ "እሳቤው ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንፃር አንድን ሀገር በጠላትነት ወይም በወዳጅነት አይፈርጅም፤ ይልቁንም ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት በትብብርና በመደጋገፍ እንዲሁም በሰላምና ልማት ዙሪያ አብሮ መስራትን ያበረታታል" ሲሉ ነው የመደመርን ሀሳብ ያብራሩት። በመሆኑም እሳቤው ለጋራ ጥቅም በጋራ መቆምን ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ ለውጤታማ ዲፕሎማሲ ሥራ ተመራጭ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል። እንደ አምባሳደር ተሾመ ገለፃ ይህ አዲስ አተያይ ከአፍሪካ አልፎ ለመላው ዓለም ሊጠቅም የሚችል አስተሳስብ ነው። የመደመርን እሳቤ ለመንቀፍም ይሁን ለመደገፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የተፃፈውን መፅሃፍ በአግባቡ አንብቦ በመረዳት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ መስጠት ጠቃሚ መሆኑን አምባሳደር ተሾመ አስገንዝበዋል። የኢህዴግን አዲስ የህብረ ብሔራዊ ፓርቲ የማቋቋም ተግባርን በማስመልክት ኢዜአ ላነሳላቸው ጥያቄም አምባሳደሩ ለዓመታት የተመከረበት እንጂ አሁን ብቅ ያለ አዲስ ሃሳብ አይደለም ብለዋል። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን በማዋሃድ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመመስረቱ ጉዳይ የድርጅቱ ነባርና አዲስ አመራሮች ሲያነሱት የነበረና ሲመከርበት የነበረ የቆየ ሃሳብ እንደሆነ አስታውሰዋል። ከውህደት ጋር ተያይዞ "ጊዜው አሁን አይደለም" ሳይሆን መባል ያለበት "የመዘግየቱ ጉዳይ ለምን?" የሚለው ነው ይላሉ። የኢህአዴግ ምክር ቤት፤ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የመራለትን የፓርቲ ውህደት ህዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ማፅደቁ ይታወቃል። የግንባሩ ሶስት ፓርቲዎችና በአጋርነት የቆዩ አምስት ፓርቲዎች ራሳቸውን በማክሰም "ብልፅግና" ፓርቲን እውን ማድርግ ችለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውህዱ ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ ዕውቅና እንዲሰጠው የውሳኔ ሃሳብ ማስተላለፉን ትናንት አስታውቋል።