ቀጥታ፡

የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለመንግስት ተቋማት የሚሰጠውን የትምህርትና ስልጠና ቅበላ መስፈርት ቀየረ

ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለመንግስት ተቋማት ሰራተኞች የሚሰጠውን የትምህርትና ስልጠና የቅበላ መስፈርት መቀየሩን አስታወቀ።

በዋናነት የፌዴራልና ክልል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የሰው ኃይል አቅም በማጠናከር ተግባር ላይ የተሰማራው ዩኒቨርስቲው የቅበላ መስፈርቱን የቀየረው በአጠቃላይ የትምህርት አሰጣጡ ላይ ባካሄደው ጥናት መሰረት መሆኑን የዩኒቨርስቲው የሥራ ኃላፊዎች  ዛሬ ገልፀዋል።

በጥናቱ ውጤትና በዩኒቨርስቲው የወደፊት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በጥናቱ መሰረት የመንግስት ተቋማቱ በዩኒቨርስቲው ለሚሰጠው የትምህርትና ስልጠና እድል ሰራተኞችን የሚመለምሉበት መንገድ ግብ ተኮር አይደለም፤ በዚህም የተነሳ ከዩኒቨርስቲው ተመርቀው የሚወጡት ባለሙያዎችን በአግባቡ እየተጠቀሙባቸው አይደለም።

የተለያዩ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ተወካዮች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እንዳሉት የመንግስት ተቋማት ወደዩኒቨርሲቲ የሚልኳቸው ሰልጣኞችን የሚመለምሉት ከብቃትና ከተገቢነት አንፃር ሳይሆን እንዲሁ በዘልማድ በጅምላ ነው።

የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ በመንግስት ተቋማት እንዲመጣ የሚፈለገውን ለውጥ እያመጣ እንዳልሆነ ነው ጥናቱ ያረጋገጠው ብለዋል።

በዚህም የተነሳ የቅበላ መስፈርቱንና አጠቃላይ የአሰራር ስርዓቱን ለመቀየር መገደዱንም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከቅበላው መስፈርት ባሻገር ከተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ሰልጣኞች የመሰልጠናቸው አስፈላጊነትና የሚጠበቀውን ግብ የመለየት ተግባር ይከናወናል።

በዚህም መሰረት ሰልጣኞቹ ከስልጣናው በፊት፣ በስልጠና ላይና ከስልጠና በኋላ የሚፈተሹበት ስርዓት መቀየሱን ነው ፕሬዚዳንቱ የሚገልፁት።

ከዚሁ ጎን ለጎም የዩኒቨርሲቲውን የትምህርትና ስልጠና ጥራትና ብቃት ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ እርምጃዎችም ይወሰዳሉ ተብሏል።

የዩኒቨርስቲው መምህራንን አቅም በማሳደግ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና የሚሰጡበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን በመጠቆም።

የዪኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዋጋሪ ነገሪ በበኩላቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች  ተገቢውን ስልጠና ለተገቢው ሰው በመስጠት ረገድ ክፍተት እንዳለባቸው በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

በመሆኑም ሰልጣኞቹም ሆኑ የሚሰሩባቸው ተቋማት ተገቢውን አቅም እንዲያገኙ ለማድረግና ከዚህም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የወደፊት የትምህርትና ስልጠና አቅጣጫ መቀየሱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዪኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ደረጃዎች ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር የአጭር ጊዜ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችንም ያዘጋጃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም