ቀጥታ፡

"የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ" በሚል በተዘጋጀው ሞጁል ላይ ምክክር እየተደረገ ነው

ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 "የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ" በሚል ለዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች በተዘጋጀው የታሪክ ሞጁል ላይ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ምክክር እየተደረገ ነው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በተቀመጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት በ2012 የትምህርት ዘመን አዳዲስ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ፕሮግራምና ኮርሶች ተቀርፀው በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በመስጠት ላይ ይገኛል።

ከነዚህ ለዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ከሚሰጡት ኮርሶች መካከል አንዱ በሆነው "የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ" ሞጁል ረቂቅ ላይ ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩም ከ48 የአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

በሚኒስቴሩ የምርምርና አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ ሚጀና እንደገለጹት፤ የታሪክ ሞጁሉ አጠቃላይ የአገሪታን ባህል፣ ቋንቋና ትውፊት በሚገልጽ መልኩ መቀረጽ አለበት ተብሎ የተዘጋጀ ነው።

የታሪክ ትምህርት ኮርሱ በሁሉም የአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ የማህበረሰዊ ሳይንስ እና ተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑንም እነዲሁ።

የኢትዮጵያ ታሪክ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደ "ኮመን ኮርስ" ለሁሉም ተማሪ እንዲሰጥ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ውይይቱም ምሁራን ሞጁሉን ቃኝተውት ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች አንዲስተካከሉና ሃሳብ እንዲሰጡበት የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የሚሰጡ ግብዓቶች ተካትተው ከሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን፣ የታሪክ ምርምር ማህበራት፣ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችና ሌሎችም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ስምምነት ላይ የደረሱበት የመጨረሻው ሰነድ ለሚኒስቴሩ የሚቀርብ መሆኑንም አክለዋል።

በውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ምሁራኑም የታሪክ ትምህርት ሞጁሉ የተማሪዎችን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በእጅጉ ለማሳደግ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይስማሙበታል።

ከኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የመጡት ወይዘሮ ትዕግስት አያሌው እንደገለጹት፤ "የታሪክ ትምህርት ሞጁሉን አስታራቂ በሆነ መንገድ እንደ አዲስ ለመከለስ የተደረገበት ሁኔታ ጥሩ ነው።"

የኢትዮጵያ ታሪክ የነገስታት እንቅስቃሴዎችን ከጦርነትና ግዛት ከማስፋፋት ጋር ብቻ የተያያዘ ተደርጎ የሚታሰብና አድሎአዊ አንደሆነ ተደርጎ የሚታመን ነበር።

ሆኖም ይህ አዲሱ የታሪክ ትምህርት ማሻሻያ ሞጁል በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የራሳችን ታሪክ ነው ብለው የሚቀበሉት ሊሆን እንደሚችልም እምነታቸውን ገልጸዋል።

የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር አቶ ማሞ ቱሚቶ በበኩላቸው፤ "አሁን ያለው ትውልድ ከታሪክ የራቀ ነው" ብለዋል።

ማንኛውም ዜጋ ከማንነት፣ ከቋንቋ እና ከባህል ጋር በተያያዘ ያሉትን የአገሩን ታሪክ በሚገባ ማወቅ ይገባዋልም ብለዋል።

ምንም እንኳን የታሪክ ሞጁሉ አንዳንድ ውዝግብ የሚፈጥሩና አላስፈላጊ ሃሳቦች ያሉበት ቢሆንም እነዚያን ነጥቦች በምሁራኑ ምክክር በመለየትና ስምምነት ላይ በመድረስ ለተማሪዎች በመስጠት ትውልዱ ታሪኩን በተሻለ መንገድ እንዲያውቀው ያግዛልም ብለዋል።

"እያንዳንዱ ትውልድ ስለ አገሩ ታሪክ በቂ እውቀት ቢኖረው የበለጠ አገራዊ ፍቅርን የሚያዳብር ይሆናል" ያሉት ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ አቶ ዲናር አማረ ናቸው።

በዚህም በሞጁሉ ላይ ከዝግጅት አኳያ ያሉ ክፍተቶች ተስተካክለው ቀርበው ተማሪዎች የራሳቸው ታሪክና የራሳቸው ባህል በውስጣቸው እንዲሰርጽ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

ውይይቱ ከዛሬ ታህሳስ 16 ቀን ጀምሮ እስከ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚካሔድም ተገልጿል።

የታሪክ ትምህርቱ ለሁሉም የአንደኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን ከሁለተኛ መንፈቅ አመት ጀምሮ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም