ቀጥታ፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ሴቶች የሉም

ኢዜአ ታህሳስ 16/2012... በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ላይ ምንም ሴቶች እንደሌሉ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት አስታወቀ። ቅንጅቱ ቀጣዩን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ''የሴቶች የፖለቲካ ታሳትፎ'' በሚል  መሪ ሐሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል። በውይይቱ መክፈቻ ላይ የቅንጅቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን እንዳሉት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ካሉ ፓርቲዎች ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ላይ ያሉ ወንዶች ብቻ ናቸው። በሌሎችም የአመራር እርከኖች ባሉ አባላት ላይም የሴቶቹ ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም በአገሪቷ ካሉ ህዝቦች 50 በመቶ የሚሆኑትን ሴቶች ተሳትፎና በአገር ጉዳይ የሚያባረክቱትን አስተዋጽኦ የሚገድብ ነው ብለዋል። በመሆኑም ፓርቲዎቹ ሴቶችን በየደረጃው ወደ አመራር ሰጪነት ለማምጣትና ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ከፖለቲካ ፕሮግራማቸው ጀምሮ ሴቶችን ለማሳተፍ አሰራር መዘርጋት አለባቸው ብለዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ አስመልክቶ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍም በሁሉም ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ መሆኑን ጠቁሟል። በጥናቱ እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ደግሞ ሴቶች ይችላሉ በሚለው ሐሳብ ላይ ፓርቲዎች ያላቸው እምነት አናሳ መሆን፣ ቀድሞ የነበረው የፖለቲካ አውድ መጥበብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ለማብቃት ፕሮግራማቸው ላይ አካተው አለመስራት የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁንና ሴቶችን በፖለቲካ ፓርቲዎች ማሳተፍ በምርጫ የህዝቡን ይሁንታ ለማግኝት፣ ሴቶች ያላቸውን እምቅ አስተሳሰብና ችሎታ ለመጠቀምና ግጭቶችን በብልሃት የመፍታት ልምዳቸውን ለመቀመር ያስችላል። የሴቶችን  የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም መድገም አለባቸው ብለዋል። በኢትዮጵያ የሴቶች ተሳትፎ በፓርላማ 38 በመቶ፣ በካቢኔ ደግሞ 50 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ቀጣዩን ምርጫ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተደረገው ውይይትም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ፓርቲ አንዳንድ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በተዳጋጋሚ ጊዜ የፖለቲካ ፓሪቲ አመራሮችን  ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ  በሚደረጉ ውይይቶች  አብዛኞቹ አመራሮች እንደማይገኙና የሚገኙትም ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው መሆናቸው ለዚህና መሰል ችግሮች መፍትሔው እንዲርቅ እድርጎታል ብለዋል ወይዘሮ ሳባ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም