የሲቪል ማህበራት ለግድቡ ግንባታ እየሰጡት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበራት ለግድቡ ግንባታ እየሰጡት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ
ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።
ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ በተለያየ መንገድ የሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በህዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ የመከረ ውይይት ዛሬ አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር እንደተናገሩት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአዲስ መንፈስና ወኔ በፍጥነት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የግድቡ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ፤ ለግደቡ ግንባታ ሕዝቡ ያደረገው የገንዘብ አስተዋፅኦ በአሁኑ ወቅት ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ጠቁመዋል።
ለዚህም ከሕዝቡ፣ ከመንግሥት እና ከንግዱ ማኅበረሰብ ቀጥሎ የሲቪክ ማህበራት የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን በመጠቆም።
ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ማህበራቱ የሚያደርጉትን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ጅማ ዲሊቦ እንደተናገሩት፤ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገሪቱ ልማት፣ ዴሞክራሲና የሰላም ግንባታ ላይ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ የሚመለከተው በታላቅ አጋርነት መንፈስ ነው።
ለዚህም ይረዳው ዘንድ አሳሪ የነበሩትን ሕጎች በማሻሻል የልማት አጋርነታቸውን አጎልብተው እንዲቀጥሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አቶ ጅማ ጠቁመዋል።
የሲቪል ማህበራቱ የሀገሪቱን የሃይል አቅርቦት ችግር በማቃለልና በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዓይነተኛ ሚና የሚኖረውን የህዳሴ ግድብ በመደገፍ ያላቸውን የልማት አጋርነት እንዲያረጋግጡም ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ አፈጻጸም ሂደትና በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ የግድቡ ግንባታ ዋና ሥራ አስኪጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ለተሳታፊዎቹ ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያለው የሶስትዮሽ ውይይትና ግንኙነት ያለበትን ሂደት የፓናል ኦፍ ኤክስፐርትስ ሰብሳቢና ተደራዳሪ ኢንጅነር ጊዲዮን አስፋው ማብራሪያ አቅርበዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀረበው ገለጻ መደሳታቸውን ገልጸው፤ የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ ይደርስ ዘንድ የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
ተሳታፊዎቹ ከመድረኩ በቀረቡት ማብራራያና ገለፃዎች ላይ መብራራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሩብ ቢለዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን አመልክቷል።
በቀጣይም ከ20 በላይ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሲቪል ሥራ ከ 85 ከመቶ በላይ መጠናቀቁም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።