የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ አዲስ የደጋፊዎች ማህበር ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ አዲስ የደጋፊዎች ማህበር ተመሰረተ
ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓም -የጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ተመሰረተ። ማህበሩን መመስረት ያስፈለገው ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችለውን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ እንደሆነ ተነግሯል። የክለቡ ፕሬዘንዳንት አቶ ሱልጣን ናስር ዛሬ በተካሄደው የምስረታ ሰነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት አዲስ የተመሰረተው የደጋፊዎች ማህበር 11 የስራ አስፈፃሚ አባላት ያሉት ነው። “ማህበሩ ክለቡን ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ለውጤት እንዲበቃ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል” ብለዋል። የደጋፊ ማህበሩ የራሱ የሆነ ጠቅላላ ጉባኤ ያለው ነጻ ማህበር ሆኖ በቋሚነት የተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል። በጅማ ከተማ ከሚገኙ 17 ቀበሌዎችና ከተቋማት የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአባልነት ያካተተና ያቀፈ እንደሚሆን አመላክተዋል ። ጅማ አባጅፋር እግር ኳስ ክለብ በ2011 ዓም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ከመቀሌ ሰባ አንደርታ ጋር በሜዳው ባደረገው ጨዋታ ባሳየው የስነ-ምግባር ጉድለት ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጭ እንዲያካሂድ ውሳኔ ተላልፎበት እንደነበር ይታወሳል። በውሳኔው መሰረት ክለቡ በዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ ከሜዳው ውጭ ጨዋታዎችን አካሂዷል። በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ከቅድስ ጊርጊስ ታህሳስ 18 ቀን 2012 ዓም ጅማ ዩኒቨርስቲ አዲሱ ስታድየም ጨዋታውን እንደሚያካሂድ በደጋፊዎች ማህበር ምስረታ ስነ- ስርዓቱ ላይ ይፋ ተደርጓል። ከወዲሁም ጨዋታውን ለሚከታተሉ የስፖርት ቤተሰቦችና ታዳሚዎች ከ30 እሰከ 200 ብር ዋጋ ያላቸው የመግቢያ ትኬቶች ተዘጋጅተው በሽያጭ ላይ መሆናቸው ታውቋል።