ቀጥታ፡

በፀረ ሙስና ትግል ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 8 ተቋማትና 9 ግለሰቦች እውቅና ተሰጠ

ኢዜአ ታህሳስ  16 /2012 የፌደራል የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፀረ ሙስና ትግል ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ስምንት ተቋማትና ዘጠኝ ግለሰቦች እውቅና ሰጠ።

የመጀመሪያው አገር አቀፍ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙሰና እውቅናና ሽልማትመርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ “መልካም ስነ ምግባርን በመገንባት፣ ሙስናን በመታገል ዘላቂ ሰላምና ልማታችንን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ ያለው።

በዚህ መርሃ ግብር ላይ በፀረ ሙስና ትግሉ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱ 8 ተቋማትና 9 ግለሰቦች ከፌደራል የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እውቅና ተሰቷቸዋል።

የእውቅናው የተሰጠው ከልማት ድርጅቶች፣ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ከመገናኛ ብዙሃንና ከትምህርት ቤቶች በሚሉ ዘርፎች ተከፍሎ ነው።

ከግለሰቦች ደግሞ የሙስና ወንጀልን በመጠቆም፣ የመልካም ስነ ምግባር ትምህርት በማስፋፋት ፣ በራሳቸው ታማኝ በመሆን፣ እንዲሁም በሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል በሚሉ ዘርፎች ተለይቶ ነው እውቅና እየተሰጠ ያለው።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ፣ አዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ የእህልና በርበሬ ወፍጮ ባለንብረቶች ፣ የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር፣ ዳይመንድ አካዳሚ እነዲሁም አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከተቋማት ተሸላሚ ሆነዋል።

ከግለሰቦች መካከል ደግሞ የሙስና ወንጀልን በመጠቆም ወይዘሮ አልታዩ ገብረየስና አቶ ቴዎድሮስ አሰጋህኝ በውሃ  ስራዎች ድርጅት  በተፈፀመ የታክስ ማጭበርበር በድምሩ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሙሰኞች እንዳይመዘበር ለመታደግ ጥቆማ አቅርበው በዚህ ጥቆማ መሰረት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ተመላሽ እንዲሁን ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ተሰቷቸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ውስጥ የተፈፀመና የገንዘብ መጠኑ በድምሩ ከ550 ቢሊዮን ብር በላይ በሆኑ 8 ጉዳዮች ላይ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ያደረጉት በዚህ እንቅስቃሴያቸው ምክንያት ለአንደኛው የሥነ ምግባርና ፀረ ሙሰና ሽልማት እውቅና የበቁት አቶ  ከፈለ ወልደ ሰማያት ናቸው።

መልካም ስነ ምግባር እንዲሰፍን በግላቸው ጥረት  በማድረግና የማስተማሪያ መመሪያ በማዘጋጀት፣ ከአንድ መቶ በላይ አስተማሪ ጽሁፎችን በማዘጋጀት እና የታነፀና የተገነባ ትውልድ ለመፍጠር ጥረት ላደረጉት መምህር ዳንኤል ጌታቸውም እውቅና ተሰቷቸዋል።

በጉምሩክ ኮሚሽን ውስጥ የሚሰሩት አቶ መንግስቱ በዳዳ የተባሉ ግለሰብ ደግሞ በኮንትሮባንድ መንግስት ሊያጣ የነበረውን ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በመታደጋቸው እውቅና ተሰቷቸዋል።

ሌላኛው በጉምሩክ ኮሚሽን ውስጥ የሚሰሩት አቶ አብዱ ይመር ደግሞ መንግስት በተጭባረበረ መንገድ  ከግብርና ቀረጥ ሊያጣ የነበረን ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የታደጉ በመሆናቸው እውቅና ተሰቷቸዋል።

አቶ መሐመድ አሚን የተባሉ ግለሰብ ደግሞ የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያቤሎ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኮንትሮባንድን በመከላከል ተግባር ላይ እያሉ በህገ ወጦች መኪና ተገጭተው በመገደላቸው ለከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ባለቤታቸው ወይዘሮ እንጉዳይ ኃይሉ የተሰጣቸውን እውቅና ተቀብለዋል።

አቶ ካሳ ተሾመ ደግሞ በሚሰሩበት መንግስታዊ ተቋም የተቋሙን አሰራር ከሙስናና ብልሹ አሰራር ለመከላከል ባከናወኑት ተግባራት እውቅና ተሰቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም