ቀጥታ፡

ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮው አገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለፀ

ኢዜአ ታህሳስ  16 /2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ከህግ ማዕቀፍ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ። የምርጫው የጊዜ ሰሌዳም በቅርቡ ይፋ ይደረጋልም ብሏል ቦርዱ።

በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሰረት በየአምስት ዓመቱ አገራዊ ምርጫ ይካሄዳል።

በዚህም መሰረት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢዜአ በምርጫው ዝግጅት ዙሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የኮሚዩኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስን አነጋግሯል።

ወይዘሪት ሶሊያና እንዳሉት ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ቦርዱ የዘንድሮውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት በማከናወን ላይ ይገኛል።

ምርጫውን ያለ ህግ ማዕቀፍ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ ተሻሽሎ የወጣውን የምርጫ ሕግ ጨምሮ ምርጫውን የተመለከቱ ሌሎች የህግ ማዕቀፎች በፓርላማ መጽደቃቸውን ተናግረዋል።

ቦርዱ የተሻሻሉትን አዋጆች በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ማከናወኑንና ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጆቹ ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡበት መደረጉን ጠቅሰዋል።

ህጉንም ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ማውጣት እንደሚጠበቅበትና ከዚህም አንጻር የተለያዩ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንና ውይይት ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል።

ከመመሪያዎቹ መካከልም በምርጫ ወቅት የሚዲያ አጠቃቀም፣ የሲቪክ ማህበራትና የክልል ምርጫ አስፈፀጻሚዎች ሚና፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳን የተመለከቱት ይገኙበታል ብለዋል።

ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫውን በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ የቦርዱን መዋቅር እስከ ክልሎች ማጠናከር እንደሚገባና በዚህ ረገድም የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት በሰባት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦርዱን የስራ ሃላፊዎች የመመደብና ተቋማዊ መዋቅርን የመከለስ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና አማራ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መስፈርቱን የሚያሟሉ ኀላፊዎች ባለመገኘታቸው ድጋሚ ማስታወቂያ ወጥቶ የማወዳደር ስራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል።

ምደባውም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አክለዋል።

የክልል ምርጫ አስፈጻሚዎች ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ ያላቸው ሚና ዝቅተኛ ነበር የሚሉት ወይዘሪት ሶሊያና የአስፈፃሚዎችን አቅም ማጠናከር ምርጫውን በጥሩ ሁኔታ ለመምራት ያስችላል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ባደረገው ድጋፍ የመራጮች ምዝገባ ህትመት ሰነዶች ግዢ መፈጸሙን አስታውቀዋል። ለሰነዶቹ ግዢ 9 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን በመጠቆም።

የመራጮች ምዝገባ ሰነዱ የደህንነትና የቴክኖሎጂ ገጽታ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም ከምርጫ ካርዶች ማባዛት፣ የመራጮች ምዝገባን በትክክል ካለማካሄድ፣ ያልተመረጡ ሰዎች ሲመርጡ ተገኙ የሚሉትን ጨምሮ በከዚህ በፊቶቹ ምርጫዎች ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን የቦርዱ ኮሚዩኒኬሽን አማካሪዋ አመልክተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ከቦርዱ ጋር ባደረገው ስምምነት ለምርጫው ማስፈፀሚያ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ገንዘብ የማሳባሰብና የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አማካሪዋ ገልጸዋል።

ቦርዱ የሰው ኃይሉን የማጠናከር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና የመስጠትና የመመዝገብ እንዲሁም በመመሪያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ይቀጥላል ብለዋል።

አክለውም የምርጫ ቁሳቁሶችን የሟሟላት ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም የኮሚዩኒኬሽን አማካሪዋ አስታውቀዋል።

የጊዜ ሰሌዳው እስካሁን ይፋ ያልሆነው ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ለምርጫው ማስፈጸሚያ ከጠየቀው አራት ቢሊዮን ብር ገደማ በጀት ውስጥ እስካሁን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈቀደው 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም 40 ሚሊዮን ዶላር ከልማት አጋሮች እያሳባሰበ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ኤጀንሲ (ዩኤስአይዲ) እና ሌሎች አጋር አካላት ለምርጫው ማስፈፀሚያ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።

ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት ከነበረው ደካማ ተቋማዊ አቅም አንጻር ባለፈው አንድ ዓመት ምርጫውን ለማስፈጸም የሚያስችለውን ጠንካራ አቅም የመገንባት ስራ ሲያከናውን መቆየቱንም ገልጸዋል።

በቦርዱ በኩል ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ እንደሆነና ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ እንደሆነም አመልክተዋል።

የቦርዱ መጠናከር ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ለምርጫው ውጤታማነት የራሳቸውን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም