ቀጥታ፡

ለምርጫው ዝግጅት እስከ ወረዳዎች አደረጃጀቶችን መዘርጋትና ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ ጀምረናል - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ኢዜአ ታህሳስ  16 /2012  ዘንድሮ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት እስከ ወረዳዎች አደረጃጀቶችን መዘርጋትና ህዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ መጀመራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። ኢዜአ ዘንድሮ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ  የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያለውን ዝግጅት በተመለከተ አነጋገሯል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የምርጫ ስትራቴጂና አስተዳደር ቡድን አባል ወይዘሮ ከውሰር እድሪስ ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ በሚገኙ 547 ወረዳዎች ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል። በዚህም ረገድ ፓርቲው በ400 ወረዳዎች አደረጃጀቱን እንደዘረጋና በቀጣይም በሌሎቹ ቀሪ ወረዳዎች አደረጃጀቱን የመዘርጋት ስራውን እንደሚቀጥል ገልጸዋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በፖለቲካ ፓርቲው ፕሮግራም(ማኒፌስቶ) ላይ ውይይት ማድረግ ባይጀመርም ፓርቲው የሚከተለውን የዜግነት ፖለቲካ አስመልክቶ ህዝብ የማወያየት ስራ እያከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል። በዋነኛነት ማህበራዊ ፍትህን መሰረት ባደረገ መልኩ ፖሊሲዎችን የማዘጋጀት ስራም እየተከናወነ ነው ብለዋል። የፖለሲ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ማስተዋወቅና ውይይት ማድረግ ደግሞ ከቀሪ ስራዎቹ መካከል እንደሆነ አመልክተዋል። የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲኖርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ፓርቲዎች በቅድሚያ ውስጣቸው ዴሞክራሲያዊ መሆን እንዳለበትና ከዚህም አኳያ ፓርቲያቸው ይሄንን ተግባር በማከናወን ላይ እነደሚገኝም ተናግረዋል። ለኢዜማ ምርጫ ሁለተኛ ጉዳይ ነው ያሉት ወይዘሮ ከውሰር፤ ዋናው ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት እንደሆነና ምርጫውም የሚካሄደው ሰላም ሲሰፍን እንደሆነ ገልጸዋል። ምርጫው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ጅማሮ እንደሆነና በቀጣይ ለመገንባት ለታሰበው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ(ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ፓርቲያቸው በምርጫ ብቻ የሚያምን ፓርቲ መሆኑን ነግረውን የምርጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን  እያከናወነ ነውም ብለዋል። ፓርቲው በተለያዩ አካባቢዎች የሚወዳደሩ የምርጫ እጩዎችን የመለየት ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል። ፓርቲው በዞንና ወረዳ በከፈታቸው ቢሮዎች የሰው ኃይል አቅሙን ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መልኩ የማደራጀት ስራ እያከናወነ እነደሆነም ገልጸዋል። ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል አደረጃጀቱን የመዘርጋት ስራ በአብዛኛው የክልሉ ወረዳዎች ማከናወኑንና ህዝባዊ ውይይቶችንም እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል። የፖለቲካ ፕሮግራሙን(ማኒፌስቶውን) ከማስተዋወቅ አኳያም ፓርቲው ራስን በራስ የማስተዳደርና ሐቀኛ የፌዴራሊዝም ስርአት መገንባት፣ ኦሮምኛ የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መስራትና የመሬት ዘረፋ እንዲቆም የሚሉ አቋሞችን ለህብረተሰቡ በውይይት እያሳወቀ እንደሆነም ተናግረዋል። አማራጭ ሀሳብ ከማቅረብ አኳያም የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ መመለስ የሚችሉ ሀሳቦች እንዳሉትና ይህ ደግሞ አማራጭ ሀሳብ መሆኑን የሚወስነው ራሱ ህዝቡ እንደሆነም አመልክተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፕሮግራማቸውን በሁሉም ቦታዎች በመዞር እንዲያስተዋውቁና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ መንግስት ሰላምና መረጋጋት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበትም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አመራሮች ገልጸዋል። የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም