16ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
16ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው
ኢዜአ ታህሳስ 16 /2012 16ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ “መልካም ስነ ምግባርን በመገንባት፣ ሙስናን በመታገል ዘላቂ ሰላምና ልማታችንን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ ያለው። በመድረኩም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ፣ የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ተዋቂ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች አርቲስቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል። በአሁኑ ሰዓትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊልምና ቲያትር ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀና በፀረ ሙስና ትግል ላይ ያተኮረ አጭር ጭውውት እየቀረበ ይገኛል። በዝግጅቱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፀረ ሙስና ትግሉ አርዓያ ለሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር የሚካሄድ ሲሆን በበዓሉ ዙሪያ አነቃቂ የሆነ ንግግርም በመጋቢ ሀዲስ እሸቱ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። “ሙስናን በመታገል የባለድርሻ አካላት ሚና፣ ያሉት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች” የሚል የመወያያ ጽሁፍም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ እንደሚቀርብ ተገልጿል። እንደ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም መረጃ በየዓመቱ በጉቦና ስርቆት ብቻ የሚፈፀም ሙስና ከ3 ነጥብ 6 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ ወደ 50 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በህገ ወጥ መንገድ ሽሽት የሚፈፀም ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ከግዢ እና ሌሎች አገልግሎት ዘርፎች ጋር ተያይዞ ከ35 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በሙስና የሚባክን መሆኑንም እንዲሁ። ይህ በሙስና የባከነ ሀብት ለመሰረተ ልማት አውታሮች፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ፣ ለጤና ተቋማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክት፣ በጥቅሉ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ቢውል ኖሮ 43 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ደሃ ህዝቦች ህይወት ይቀየር እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ።