መገናኛ ብዙሃን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሙያ ጣልቃገብነት አለባቸው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሙያ ጣልቃገብነት አለባቸው ተባለ
ኢዜአ ታህሳስ 15 /2012 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በግለሰቦችና በቡድኖች የሚደርስባቸው ጣልቃ ገብነት የሙያ ነጻነታቸውን እንዳሳጣቸው ተገለጸ። ይህ የተባለው ዛሬ 'የሚዲያ ሚና አሳቦችን ለማቀራረብ' በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በየወሩ የሚካሄደው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ሲካሄድ ነው። በዚሁ ጊዜ መገናኛ ብዙሃን እንደ አገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ ሚና ሲጫወቱ መቆየቱ ነው የተገለጸው። ''ሚዲያ በሽግግር ወቅት'' በሚል ርዕስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ የውይይት መነሻ ጥናት አቅርበዋል። በጥናታቸውም በኢትዮጵያ የህዝብና የግል መገናኛ ብዙሃን በግለሰቦችና በቡድኖች በሚደርስባቸው ጫና የሙያ ነጻነታቸውን እያሳጣቸው መሆኑን ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት። በአሁን ጊዜ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ቢሆንም ከመንግስት ባለፈ ከግለሰቦችና ከቡድኖች በሚደርስ ጫና የሙያ ነጻነነት እየቀጨጨ መምጣቱን ዶክተር ሙላቱ ተናግረዋል። በተለይ የጸር ሽብር አዋጁ መጽደቁን ተከትሎ በአገሪቱ የሚዲያ ታሪክ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን አስታውሰዋል። በአገሪቷ አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃን የዴሞክራሲ ስርዓትን ከማጠናከር አኳያ ክፍተቶች ያሉባቸው ሲሆን ግጭትን ከማርገብ ይልቅ ማባባስ ላይ የሚጠመዱ ናቸው ብለዋል። እንደ ዶክተር ሙላቱ ገለጻ፣ የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ የፖለቲካ ሀሳቦችን ከማንሸራሸር ይልቅ ገዥውን ፓርቲ የሚያንቋሽሹና የሚኮንኑ ዘገባዎች ማቅረብ ላይ የተጠመዱ ናቸው። ይሁንና ብሄር ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰራጩ አሉታዊ ዘገባዎች በአገሪቷና በህዝቦቿ ላይ የከፋ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው። አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃን ግልጽ የሆኑ የጥላቻ ንግግሮችን የሚጠቀሙ መሆኑንና የሀሳብ ብዝሃነት ላይ ትኩረት እንደማያደርጉም በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የአቅም ውስንነትና ጠንካራ የሙያ ማህበራት አለመኖር የሙያውን ስነ-ምግባር ተከትሎ ሚዛናዊ ዘገባ እንዳይቀርብ ማድረጉንም ዶክተር ሙላቱ አንስተዋል። የህዝብና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በአሁን ጊዜ አራት አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉም ዶክተር ሙላቱ ያስረዳሉ። በውይይቱ ላይ የግል መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በአሁን ጊዜ በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሉ ያሉትን ችግሮች አንስተዋል። በጭፍን መደገፍና መቃወም፣ ተመሳሳይ የሆነ ምንጭ መጠቀም፣ ሚዛናዊነትን ጠብቆ ያለመስራትና ተጠያቂነትን አለመፍራት የመገናኛ ብዙሃኑ ችግር ሆነው እየታዩ እንደሆነ ጠቁመዋል። '