ለረጅም ዓመት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የስፖርት አካዳሚ እያረጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለረጅም ዓመት አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የስፖርት አካዳሚ እያረጀ ነው
ኢዜአ ታህሳስ 15 / 2012 ከስምንት ዓመት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ ዝግ ሆኖ የተቀመጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የልህቀት አካዳሚ ህንጻ እያረጀ መጥቷል።
አካዳሚው እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት ሳይሰጥ የቀረው በባለቤትነት የሚከታተለው አካል እንደሌለ በቅርቡ አካዳሚውን እንዲመሩ የተሾሙት ዳይሬክተር ተድላ ዳኛቸው ገልጸዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ ከ15 ዓመት በፊት የእግር ኳስ የልህቀት አካዳሚ ለመክፈት በአህጉሩ ካሉ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን፣ ካሜሮንና ሴኔጋልን መርጦ ነበር።
ከሦስቱ የእግር ኳስ የልህቀት አካዳሚዎች ውስጥ የካሜሮን አካዳሚ ግንባታው ተጠናቆ ስራ ከጀመረ ከስድስት ዓመት በላይ ሆኖታል።
የሴኔጋልም በተመሳሳይ በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በኢትዮጵያ የካፍ የእግር ኳስ አካዳሚ ግንባታ በ1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አያት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነበር ግንባታው የተጀመረው።
ግንባታው ሲጀመር ደግሞ በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ ነበር የታቀደው።
አካዳሚው ሦስት የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ 40 የመኝታ ክፍሎች፣ የምግብ ማብሰያ ቦታዎችና ለሌላ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎችንም ያካተተ ነው።
የእግር ኳስ ሜዳዎቹ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ሳር የተሸፈኑ ሲሆን በአካባቢው በቂ ውኃ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ የሜዳዎቹ ስራ ማጠናቀቅ አልተቻለም።
40 የመኝታ ክፍሎች፣ የምግብ ማብሰያ ቤትና ሌሎች ለእግር ኳስ ስልጠና ቆይታ አጋዥ ናቸው የተባሉ ስራዎች የተጠናቀቁት ግን በ2004 ዓ.ም ነበር።
የአካዳሚው የውስጥ ግንባታ ደረጃቸውን በጠበቁ ዕቃዎች የተሰራ ሲሆን ህንጻው አገልግሎት ሳይጀምር የመስተዋት መሰበባር፣ የጣሪያ ማፍሰስና ሌሎች ለአካዳሚው አገልግሎት አጋዥ የሆኑ ዕቃዎች መሰበባር፣ እንዲሁመ ብረት ነክ የሆኑ ዕቃዎች ደግሞ ለዝገት ተዳርገዋል።
ካፍ ባለፈው ዓመት አካዳሚውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስተላለፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ አካዳሚውን የሚቆጠጣርና የሚከታተል ባለሙያ ከሁለት ወር በፊት ቀጥሯል።
የአካዳሚው ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት እጩ ዶክተር ተድላ ዳኛቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ "አካዳሚው እስከ አሁን ድረስ አገልግሎት ሳይሰጥ የቀረው በባለቤትነት የሚከታተለው አካል ባለመኖሩ ነው" ይላሉ።
''በዚህ ምክንያት ህንጻው አገልግሎት ሳይሰጥ አርጅቶ ተጨማሪ የጥገና እና የዕድሳት ስራ አስፈልጎታል'' ብለዋል።
አካዳሚው ጥገና እና እድሳት ካልተደረገለት ሜዳዎቹ ለስልጠና አመቺ እንዳልሆኑ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ አካዳሚው ጥገናና እድሳት ተደርጎለት ወደ ስራ ማስገባት ከተቻለ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተጨማሪ የገቢ አቅም ከመፍጠርም በላይ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬም ገቢ ማስገኘት ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የውድድር መዘጋጃ ጊዜውን በሆቴል በማረፍ የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ረገድም እንደ አማራጭ መጠቀም ይቻል ነበር።
የኢትዮጵያ ወንዶች፣ ሴቶችና ታዳጊ ወጣቶች ብሄራዊ ቡድኖች ለአንድ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ቅድመ ዝግጅት ከብር 800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ለሆቴል ወጪ እንደሚወጣ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ብሔራዊ ቡድኖቹ ለአፍሪካ ዋንጫ፣ ለቻን እና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በአገር ውስጥ ለቅድመ ዝግጅት የሚወጣው ወጪ በዓመት በአማካይ እስከ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብርም ይደርሳል።
የአካዳሚው ስራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምር ታዲያ ለብሔራዊ ቡድኖቹ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ይቻል ነበር።
በ1997 ዓ.ም የተጀመረውና በ2000 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበው የእግር ኳስ አካዳሚው ግንባታው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥቅሞችን እያሳጣ ይገኛል።
አካዳሚው ጥገናና እድሳት ተደርጎለት ወደ ስራ ለማስገባት የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን /ፊፋ/ ለእግር ኳስ ልማት ድጋፍ ከሚያደርገው ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ለመጠቀም የትልመ ሀሳብ /ፕሮፖዛል/ የመቅረጽ ስራ መጠናቀቁንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከፊፋ የሚገኘው ገንዝብ በቂ ስለማይሆን ሌሎች ድጋፍ የሚያድርጉ አካላት ትብብር እንዲያደርጉም የሚሰራ ስራ ይኖራል።
የአካዳሚው ግንባታ ሲጀመር ካፍ በኢትዮጵያ በኩል ግንባታው እንዲከታተሉ በኃላፊነት የሾመው የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ሳህሉ ገብረወልደን እንደነበረ ይታወሳል።