እውነትም መደመር ውበትን ያጎናጽፋል!

56
አዲሱ ረታ-ኢዜአ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በብዙዎቹ የለውጥ ናፋቂዎችና ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያኖች ዘንድ እጅግ ስትናፈቅ የቆየች ቀን ነበረች። ለአንድ ሳምንት ገደማ አብዛኛው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ወጣት ስለዚች ቀን ታሪካዊነት ሲጽፍ፣ ሲያጋራና ሃሳብ እያንሸራሸረ የጠበቃት ቀን ናት። ከሁሉም በላይ በዋዜማው የተደረገው ሽር ጉድ እጅግ ብዙዎችን ለአንድነትና ለኢትዮጵያዊነት ማነሳሳቱ እሙን ነው። በዚሁ ቀን ጧት 12 ተኩል ገደማ ነበር። እኛም ለታቀደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ የሚዲያ ሽፋን ለመስጠት ከመስሪያ ቤቴ ባልደረቦች ጋር እንቅስቃሴ ጀመርን። ገና መስሪያ ቤቱ መውጫ በር ላይ ስንደርስ መንገዱ ባልተለመደ ሁኔታ በመኪና ተሞልቶ ነበር። አብዛኞቹ ከሱሉልታ የሚመጡ የድጋፍ ሰለፉ ታዳሚዎች ነበሩ። እኛም እነሱን ተቀላቀልን፤ ጉዟችንንም ወደ መስቀል አደባባይ አደረግን። ሰልፉ የተዘጋጀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዉያንን ልብ መግዛት መቻላቸውና አንድነትን ይበልጥ በመስበካቸው፣ እሳቸውን የማበረታታትና 'ከጎንህ ነን' ቀጥልበት ለማለት ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ መሰበሰብ አስፈልጓቸው ነበር። መሪ ቃሉም 'ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበረታታ' የሚል ነበር። ማለዳ አንድ ሰዓት መስቀል አደባባይ ስንደርሰ አደባባዩ በኢትዮጵያውያን አሸብርቆና ደምቆ ነበር። መስቀል አደባባይ በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሯቸው ንግግሮች ተሰቅለዋል። በተለይ ደግሞ 'እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን' የምትለው ሀረግ በሁሉም የአደባባዩ አቅጣጫ ሊባል በሚችል መልኩ ተሰቅላለች። መስቀል አደባባይን በዛ ጠዋት፣ የአዲስ አበባ ብርድ ያልበገረው ለውጥ ናፋቂ ሰልፈኛ ሞልቶታል። በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ሰልፈኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል የታተመባቸውን ቲ ሸርቶች ለብሰዋል። በተለይ ደግሞ ፈገግ የሚያሰኘው ነገር፣ የጠቅላይ ሚስትሩ ምስሎች እንደየ ሰልፈኛው ፍላጎትና ባህሪ ጋር እንዲጣጣሙ ተደርገው ነው የታተሙት። ለምሳሌ አንድ ታዋቂ ወጣት የ'ራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ' በለበሰው ቲ ሸርት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራፐር መስለው ይታዩ ነበር። ሌሎች እንዲህ አይነት ምስሎች በስፋት ታይተዋል። ሌላው በጣም የሚገርመው በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ሰልፈኛ 'መደመር' የሚል ቃል የተጻፈባቸው ቲ ሸርቶችን ለብሰዋል። ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት የሚሉ ቲ ሸርቶች፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ የሚል ጽሁፍም በስፋት ነበር። ከዚህ ጎን ለጎን ይዘው የወጡት መፈክሮችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ግራፍ ያሸበረቁ ነበሩ። የፎቶ ግራፍ ነገር ከተነሳ አይቀር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የአቶ ለማ መገርሳ ፎቶ ግራፍና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፎቶዎች በስፋት በሰለፈኛው የተያዙ ሲሆን ሌሎች ማንነታቸውን ያላወኳቸው ሰዎች ፎቶዎችም ሰልፉ ላይ ተስተውሏል። ከሁሉም ግርምትን የሚፈጥረው የኢፌድሪ መንግስት በይፋ ከሚጠቀመው ሰንደቅ አላማ ጀምሮ ከተወሰኑት በስተቀር ማንንና የትኛውን አገር እንዲሁም የትኛውን ቡድን እንደሚወክሉ ያላወኳቸው ሰንደቅ ዓላማዎች ሲውለበለቡ ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ህዝቦችን እርስበርስ ሊያቃርኑ የሚችሉ መፈክሮችም ተይዘው ነበር። ስልፉ ላይ አቅመ ደካሞች፣አዛዉንቶች በቲሸርትና በመፈክር ደምቀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን አድናቆትና ቀጣይ ድጋፍ ሲገልጹ ነበር። ከፍተኛ ቍጥር የሚይዘው ወጣቱ የሕብረተሰብ ክፍል ቢሆንም ታዳጊዎች፣ አልፎ አልፎ ህጻናትም በተለያዩ ቀለማት አሽብርቀው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ ነበር። በጥቅሉ የዛሬ ሰልፍ ላይ ቀረ የሚባል የህብረተሰብ ክፍል የለም። እኔ በበኩሌ ለካ ኢትዮጵያዊያን ሲደመሩ ውብታቸው ይጨምራል አስብሎኛል። ሰልፈኛው ፍጹም ሰላማዊ ነበር። በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ የአንድነት መንፈስ እየመጣ መሆኑንም ማንም መረዳት ይችላል። ግን... አሁንም ያልተገሩ አስተሳሰቦች በስፋት ይስተዋላሉ። ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስል ይቅር መባባል የተሰለፈው ህዝብ ማሃል አሁንም ልዩነትን የሚያጎሉ ክስተቶች ነበሩ። ምንም እንኳን የሰለፉ አስተባባሪ ኮሚቴ 'ምንም አይነት የተለየ ፍላጎት የማይንጸባረቅበት ሰልፍ ይሆናል ' ቢልም በጥቂቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞትና ፍላጎቶች በተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ሲደረጉ ነበር። የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ... ኮከብ የሌለው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል። ጥቂት ወጣቶች 'ትክክለኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይህ ብቻ ነው' ሲሉም ተደምጠዋል። በእኔ እምነት ይህ ሁነት ችግር ላይኖረው ይችላል። ግን ደግሞ ለሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አያስፈልገውምን?  ማለት እፈልጋለሁ። ከዚህ ውጪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰንደቅ ዓላማ እዚህም እዛም ይታይ ነበር። ሌሎች ሰንደቅ ዓላማዎችም ነበሩ። ለምን በዚህ ቀን አስፈለገ?  አሁንም የአስተሳሰብ አንድነት ላይ እንቅፋቶች ለመኖራቸው ማሳያ ነው። ሌላው ጉዳይ... በሰልፉ ወቅት ከመድረክ ላይ ስለ መደመር ሲወራ በደስታ የሚያጨበጭብ፣ የሚጮህ ሰልፈኛ ድምጹ ያስተገባል። ስለ አንድነት፣ ስለ ሰላምም እንዲሁ ግን ደግሞ፣ በወቅቱ የተለቀቁ የተወሰኑ ዘፈኖች 'ለምን እዚህ ተከፈቱ' በሚመስል መልኩ በጥቂቶች የተቃውሞ ምልክቶች ታይተዋል። ይህ ምን ማለት ነው?  ስለ ይቅርታ ሲወራ፣ ስለ መደመር ሲወራ በመግባባት የሚያጨበጭብ ህዝብ እንዴት እዛው ጥላቻን ያንጸባርቃል? አሁንም ለእኔ አንድነትን የተረዳንበት መንገድ ላይ ችግሮች አሉ አስብሎኛል። አሁንም የሚያስተዛዝበው ጉዳይ... ስለ ጥላቻ መጥፎነት 'ተረድቼያለሁ ከዚህ በኃላ እዚህ ሰፈር አልገኝም' ባለው ሰልፈኛ መሃል የተወሰኑ ቡድኖችና ግለሰቦችን ስም እየጠሩ የጥላቻ ስድቦችን ሲያዥጎደጉዱ የነበሩ ሰልፈኞችም አልታጡም። የሆነው ሆኖ ግን ሰልፉ እስከተቋረጠበት ቅጽበት መስቀል አደባባይ እጅግ ተውባና ደምቃ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከፍ ብሎ ታይቶባታል። ህዝቡ ምን ያህል አንድነትን አጥብቆ እንደሚሻ ማወቅ ይቻላል። በእኔ ግምት እጅግ ከጥቂቶች በስተቀር ሰልፈኛው ሰላማዊና እውነትም ከልቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ የወጣ ነበር። መጨረሻ ላይ የጸጥታ አስከባሪዎች እጅግ በሰለጠነ መንገድ ሰልፈኛውን ሲያስተባብሩ እንደነበረ መታዘብ ችያለሁ። ይህም ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ ነው። ለሞቱትና ለተጎዱት ፈጣሪ ምህረቱን ይላክላቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም