ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በሞጣ በተከሰተው ግጭት ለተጎጂዎች ካሳ እንዲከፍልና ጥፋተኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ መንግስትን ጠየቀ

ኢዜ አ ታህሳስ 15/2012  የአማራ ክልል መንግስት ከሰሞኑ በሞጣ የተከሰተውን የግጭት መንስዔና የደረሰውን ጉዳት አጣሪ ኮሚቴ እንዲደግፍና ጥፋተኞችንም ለፍርድ እንዲያቀርብ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠየቀ።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱን በማውገዝና ተጎጂዎችን ለማጽናናት ላደረጉት ሚናም አመስግኗል። ምክር ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ መነሻው ባልታወቀ ምክንያት በመስጊዶችና በንግድ ተቋማት ላይ በደረሰው ቃጠሎና ዘረፋን በማውገዝ፣ የችግሩን ምክያትና ጉዳት መጠን የሚያጣራ ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታውቋል።

ድርጊቱ ኃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ ህግን ፍጹም የሚጻረር እንዲሁም አብሮነትና የመተሳሰብ ባህልን የሚንድ ተግባር መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተፈጸመውን ድርጊት በማውገዝና ተጎጂዎችን ለማጽናናት ላደረጉት ሚና ያለውን ምስጋና ገልጾ፤ በቀጣይም የጋራ ኃላፊነት እንወጣ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ለአማራ ክልል መንግስት አምስት ጥያቄዎቸን በአፋጣኝ ምላሽ ይሰጠኝ ሲል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የችግሩ መንስዔና የደረሰውን ጉዳት አጣሪ ኮሚቴ እንዲደግፍና ያቃጠሉ አካላትን ለፍርድ እንዲያቀርብ አሳሰቧል።

እንዲሁም ለድርጊቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ ብሎም በድርጊቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም በክልሉ ያሉ ሙስሊሞችን ችግር የሚፈታ ኮሚቴ አዋቅሮ ወደ ተግባር እንዲገባ የሚሉ ይገኙበታል።

ምክር ቤቱ የጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካላገኙም ታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም