የላሊበላ የገና በዓልን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ለማስፈር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የላሊበላ የገና በዓልን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ለማስፈር እየተሰራ ነው
ኢዜ አ ታህሳስ 15/2012 የላሊበላ የገና በዓልን በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ላይ ለማስፈር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገለጸች። በመላው ዓለም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በየዓመቱ በታህሳስ ወር ተከብሮ ይውላል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያንም ከ9ኙ አበይት በዓላት አንዱ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በተለይም በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በታላቅ ድምቀት የሚከበር ኃይማኖታዊ በዓል ነው።
ዕለቱም የቅዱስ ላልይበላ (ላሊበላ) የልደት ቀን ከኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር የተሳሰረ በመሆኑ በስፍራው ደማቅና ማራኪ በሆነ መንገድ የሚከበር መሆኑንም የታሪክና የኃይማኖት ድርሳናት ያስረዳሉ።
በዓሉ በስፍራው ባሉ አብያተ ክርስትያናት የሚገኙ ካህናት፣ ከየአካባቢው የመጡ ምዕመናን፣ የተለያዩ አገራት ቱሪስቶችና ብጹአን አባቶች በተገኙበት ይከበራል።
በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምዕመናን አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዓቱን ለመጎብኘትና ለማክበር ወደ ስፍራው ይጓዛሉ።
ጥንግ ድርብ በለበሱና ማዕጠንት የያዙ ሊቃውንት፣ ካህናትና ዲያቆናት የወርቅ ካባ ለብሰው፣ የወርቅ አክሊል ደፍተው፣ የወርቅ መስቀል ይዘው መለከት እየነፉ ዙሪያውን በመዞር ማህሌቱን ያጅቡታል።
በዓሉ እንዲህ ባለ ሁኔታ መከበር ከጀመረ 900 ዓመትትን ያስቆጠረ ሲሆን ይህን ታላቅ በዓል በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገልጻለች።
የቤተክርስቲያኗ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብጹእ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኃይማኖታዊ በዓላት ለዓለም ማህበረሰብ ማስተዋወቅናና እንክብካቤ ማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ነው።
በዚህም ቤተክርስትያኗ ካሏት ሃብቶች አንዱ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል (ገናን) ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ቤተክርስትያኗ በርካታ የዓለም ቅርስ መሆን የሚችሉ ሃብቶች እንዳሏት የገለጹት ብጹዕ አቡነ አረጋዊ፤ በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓልም ለዘመናት ኃይማኖታዊ ስርአቱን ጠብቆ ሳይዛነፍ ለትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ይህም የአለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ቢመዘገብ የአለምን ህዝብ ትኩረት ይበልጥ ለመሳብ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል።
በዓሉ ከኃይማኖታዊነቱ ባሻገር ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውና ለአገር ገጽታ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳም ከፍተኛ መሆኑንም ያስረዳሉ።
በቅርቡ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የጥምቀት በዓልን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የመስቀል ደመራ በዓል፣ የገዳ ስርዓትንና የፊቼ ጫንበላላ በዓልን በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት መስመዝገብ ችላለች።