ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ ወደ ሀብት የመቀየሩ ስራ እየተሰራ ነው - ኤጀንሲው - ኢዜአ አማርኛ
ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ ወደ ሀብት የመቀየሩ ስራ እየተሰራ ነው - ኤጀንሲው
ኢዜአ ታህሳስ 15/2012.. ለጤና ጠንቅ የሆነውን ቆሻሻ በአግባቡ ለማስወገድና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋልም ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ለአብነትም ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መገንባቱ ይታወሳል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ለማ እንዳሉት ደረቅ ቆሻሻን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ባለሙያዎች ጃፓን አገር ሰልጥነው የመጡት ሌሎችን እንዲያሰለጥኑ መደረጉን ተናግረዋል። የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ የከተማዋ 60 በመቶ ቆሻሻ በየቀኑ የሚወገድበት ቦታ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጭውን ተሞክሮ የወሰዱ ባለሙያዎች ለሌሎች ስልጠና በመስጠት ቆሻሻን በአግባቡ መልሶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በጃፓን አገር ሰልጥነው የመጡ ባለሙያዎች የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተሰራው ስራም በቆሼ እስከ 50 ሜትር ርዝመት የነበረውን ቆሻሻ ክምር በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል መቻሉንም ገልጸዋል። ቆሻሻው በአካባቢ ላይ ብክለት እንዳያስከትልና እንዳይደረመስ የሚያስችል የተለያዩ ተግባራት መከናወኑንም ጠቁመዋል። በመሆኑም ቆሻሻው አካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በተለያዩ ቴክኖጂዎች አማካይነት ስራ ላይ እየዋለ ይገኛልም ብለዋል። የኤጀንሲው የላንድ ፊል ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ሲሳይ በበኩላቸው የረጲ-ቆሼ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃን አሁን ዘመናዊ በሆነ መንገድ እያለማን ነው ይላሉ። በቀጣይም ቆሻሻ ማስወገጃውን ወደ አረንጓዴ ቦታ ለመቀየር የሚያችል ስራ እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል። ስልጠና ከወሰዱ ሰራተኞች መካከል አቶ ሰርካለም ዘነበ እንደሚለው በፊት በነበራቸው ልምድ ላይ አሁን ያገኙትን ዘመናዊ ክህሎት በማጣመር በተግባር እንደሚያውሉ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የቆሻሻ ክምር ተደርምሶ በሰዎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።