የዞኑ የሃይማኖት ተቋምት ጉባኤ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የዞኑ የሃይማኖት ተቋምት ጉባኤ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት አወገዘ
ታህሳስ 15/2012 የደቡብ ወሎ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት አወገዘ። የደቡብ ወሎ ዞን የሀይማኖቶች ተቋም ሰብሳቢና የሐገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ሊቀ መምህር ብርሃነ ህይወት እውነቱ ትናንት በተሰጠው የጋራ መግለጫ እንዳሉት በኢትዮጰያ ሁሉም ሐይማኖቶች ተቻችለውና ተከባብረው በመኖር ላይ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ ''ሰሞኑን በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማትና የንግድ ቦታዎች ላይ የደረሰው ጥቃት የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶቻችን ለመሸርሸር በጥቅመኞች የተሸረበ ሴራ ነው'' ብለዋል፡፡ ''የእምነት ተቋማት ሊከበሩ፣ ሊጠበቁና ሊፈሩ ይገባ ነበር'' ያሉት ስራ አስኪያጁ ከማንኛውም እምነት ውጭ የሆኑ ግለሰቦች ሞጣ ከተማ ላይ ያደረሱት ጉዳት ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ''አሁንም ቢሆን የበላይና የበታች ሐይማኖት ባለመኖሩ ወጣቱ ሰከን ብሎ፣ ተደማምጦና አንድ ሆኖ አጥፊዎችን ለህግ አሳልፎ መስጠት ይጠበቅበታል'' ብለዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የሐይማኖት ተቋሙ ምክትል ሰብሳሰቢ ሸህ ከድር ሁሴን በበኩላቸው ማንኛውም የእምነት ተቋማት ክቡር ናቸዉ፡፡ ይሁን እንጅ አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የእምነት ተቋማትን በድፍረት ማቃጠል ከማንኛውም እምነት አለኝ ከሚል ግለሰብ የሚጠበቅ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም "ሁላችንም ከስሜት ርቀን ማስተዋልና የማይለያዩ እምነቶችን ለመለያየት የሚሰሩ የጥፋት ኃይሎችን ለህግ አሳልፈን በመስጠት አገራዊ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡ መንግስትም በየጊዜዉ ''አልታገስምና ተጠርጣሪዎችን እየያዝኩ ነዉ'' ከሚሉ መግለጫዎቹ ተላቆ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት በማሳለፍ ህብረተሰቡን መካስ እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያን ተወካይና የሐይማት ተቋሙ ጸሐፊ ፓስተር ስለሽ አሊጋዝ በበኩላቸው ''በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የተከሰተዉ ድርጊት አሳዛኝ ነው'' ብለዋል። ህብረተሰቡን ለማለያየት ሆን ተብሎ የተሰራ ተንኮልና የኢትዮጵያን ባህል የማይገልጽ በመሆኑ ሊወገዝ የሚገባው ነውረኛ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ''የተቃጠሉ መስጅዶች እንዲሰሩና የተጎዱ ወገኖች እንዲካሱ መንግስት መስራት አለበት'' ያሉት ፓስተሩ የሁሉም እምነት ተቋማት ለአገር አንድነትና ሰላም የድርሻቸዉን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ሌላዉ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተ ክርስቲያን መካነየሱስ ተወካይና የሐይማኖት ተቋሙ አባል ቄስ ዘለቀ ይመር እንደገለጹት ይህን አስቸጋሪ ወቅት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን አንድነታችን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ መታደግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ''ከሚያለያየን ጉዳዮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ስለሚበዙ ልዩነታችንን አጥብበን ወደ አንድ መምጣትና አጥፊዎችን አሳልፎ መስጠት ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡ ''እንዲህ አይነት አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊቶችንም በየእምነት ተቋማችን ማውገዝና ህብረተሰቡን ማስተማር ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በተፈጠረው ችግር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለሀግ የማቅረቡ ስራ እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል፡፡