መንግስት ለቤተ እምነቶች ጥበቃና የህግ ከለላ እንዲያደርግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለቤተ እምነቶች ጥበቃና የህግ ከለላ እንዲያደርግ ተጠየቀ
ኢዜአ ታኅሣሥ 14 ቀን 2ዐ12 ለሃገር ባለውለታ በሆኑ ቤተ እምነቶች ላይ እየተስተዋለ ያለውን ጥቃት ለመከላከል መንግስት ተገቢውን ጥበቃና የህግ ከለላ እንዲያደርግ የኃይማኖት አባቶች ጠየቁ።
የኃይማኖት አባቶቹ ጥያቄውን ያነሱት በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክተው ትላንት ከመንግስት አመራር አካላትና የአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰዒድ አህመድ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያዊያን የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው አንዱ የአንዱን ቤተ እምነት ሲገነቡ የኖሩ ናቸው።
ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የእምነት ተቋማትን ማዕከል ያደረገና አንዱ በሌለኛው እምነት ተከታይ ላይ በማሳበብ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አውስተዋል።
የእስልምና እምነት አስተምህሮ የሚተገብር ሙስሊም ቤተክርስቲያንን የሚያቃጥል ሳይሆን ቤተ ክርስቲያናት ሲሰሩ በጉልበቱና በገንዘቡ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።
የክርስትና እምነት ተከታዮችም እንዲሁ እንጂ ጉዳት ሊያደርሱ ቀርቶ አስበውትም እንደሚያውቁ ገልጸዋል።
ለረጅም ዘመናት ሲረዳዳ የኖረውን ህዝብ በኃይማኖት ሽፋል ለመከፋፈልና የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ቤተ-እምነቶችን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።።
በሁለቱም የእምነት ተቋማት የሚደርሰው ጥቃት ሙስሊሙንና ክርስቲያንን እንደማይወክሉ ሼህ ሰዒድ ተናግረዋል።
መንግስት ህዝብን በእምነት ምክንያት የሚከፋፈሉ አካላትን ስርዓት በማሲያዝ ቤተ በእምነቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥበቃና የህግ ከለላ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብጽኡ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው የእምነት ተቋምት ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በሃገሪቱ ሰላምና ልማት እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም አጋርና ተሳታፊ መሆናቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ የሃገር ባለውለታ የእምነት ተቋማት በማንኛውም መንገድ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደማይገባና መንግስት ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።
"የትኛውም እምነት አብሮ መኖርን እንጂ መለያየትን አያበረታታም "ያሉት አቡነ ዮሴፍ ልዩነትን የሚሰብኩና ጥፋትን የሚያውጁ አካላትትን አስተማሪ የሆነ ህጋዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት መጠየቅ እንደሚገባም አመልከተዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገር እንዳሉት ህዝብን ሰላም ለመንሳት ብሄርን መሰረት ያደረጉ ሴራዎች ለበርካታ ዓመታት ቢሰራም አልሳካ ሲል ጉዳዩን ወደ እምነት ለማዞር ታቅዶ እየተሰራ ነው።
በኃይማኖት ሰበብ ህዝብን ለመለያየት በሚሰሩና ተልኮ አስፈጻሚ አካላት ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።
"የአማራን ህዝብ ለመለያየት የተሰሩ ሴራዎች የበለጠ እያጠናከሩት ይሄዳሉ እንጂ አይለያዩትም "ያሉት አቶ አገኘው በሞጣ ከተማ የእምነት ተቋማት ላይ ጥፋት ያደረሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጸው፣ የኃይማኖት አባቶች በእምነት ሽፋን ብጥብጥ የሚፈጥሩ አካላትን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።