ቀጥታ፡

የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 80 በመቶ ተጠናቀቀ

ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓም -የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ስራ 80 በመቶ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ። የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር ፓርኩን ፈጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት አላማ ያደረገ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በወቅቱ እንደገለጸት የክልሉ የልማት ድርጅቶች በተደራጀ መንገድ በፓርኩ ግንባታ በመሳተፋቸው ስራው 80 በመቶ ተጠናቋል ። የፓርኩ የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታ በ260 ሄክታር መሬት ላይ ማረፉንና የማምረቻ፣ የአገልግሎት መስጫ፣ የማከማቻና ሌሎች ህንጻዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የመብራት፣ የውሃና የቴሌ መስመር ዝርጋታዎችና የ12 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ በተቀናጀ አግባብ በጥራትና በፍጥነት መገንባታቸውን ተናግረዋል። ግንባታው ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ መኖሪያና ሌሎች ለሰራተኞች አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎት መስጫዎች የተሟሉለት በመሆኑ ለሰራተኞች ምቾትና ደህንነት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል ። ፓርኩ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግና የኢንዱስትሪ እድገትን ለማረጋገጥ አስተዋጻው የጎላ እንደሆነ አመላክተዋል። ፓርኩ የተገነባበትን አላማ ለማሳካት ከአርሶ አደሩ አመራረት ጀምሮ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በማዘመን በኩል ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ኃላፊው አሰገንዝበዋል ። "የገንዘብና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረትን በመቅረፍ ፓርኩን ፈጥኖ ወደ ስራ ማስገባት ይኖርብናል" ብለዋል ። የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደሴ አሰሜ በበኩላቸው የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክ በክልሉ ለመገንባት ከታቀዱ ሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። ለፓርኩ ግብአት የሚያቀርቡ ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላት በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ከማዕከላቱ መካከል ቀደም ሲል በሞዴልነት የተጀመረው የሞጣ ማዕከል ግንባታ ከ85 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "በፓርኩ ግንባታ ስራ ከ3ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል" ስራ አስፈጻሚው ወደ ምርት ሲሸጋገር ከ20ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የስራ እድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል። "ፓርኩን ብቃት ባለው የሰው ኃይል በማደራጀት ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ አቶ የሻምበል ከበደ ናቸው። በክልሉ 119 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዳሉ ጠቁመው ፓርኩ የሚፈለገውን የሰው ኃይል ከወዲሁ ለማሟላት ዘርፎችን በመለየት 150 ሰዎች እየሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ የገጠር ልማት ስትራቴጅና ሞዴል መንደር ማማከር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መልኬ ታደሰ በበኩላቸው "ፓርኩ ስራ ሲጀምር አርሶ አደሩ ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል" ብለዋል ። አዳዲስ አሰራሮችን በመተግባር እንዲሁም የተሻሻሉ ግብዓቶችን በመጠቀምና በመስኖ በመታገዝ አስተማማኝ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ። "መንግስት የአመራረት ዘይቤን ለማዘመን የሚያስችሉ የእርሻ ማሽኖች ከቀረጥ ነጻ ከውጭ የሚገቡበትን ሁኔታ እያመቻቸ መሆኑ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ነው" ብለዋል። የደቡብ ኮሪያ የገጠር ልማት ያስገኘውን ለውጥ በክልሉ ለመተግበር በፕላስቲክ በተሸፈነ ትንሽ ቦታ ዓመቱን ሙሉ የማምረት ልምድና ባህልን አርሶ አደሩ እንዲያጎለብት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ለቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክና ለሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላት ግንባታ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ መደረጉን የገለጹት አስተባባሪው  ግንባታው ለሌሎች ተሞክሮ በሚሆን መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። በምክክር መድረኩ የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎችንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም