ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ
ኢዜአ ታህሳስ 14/2012 መደበኛ ባልሆነ የኢኮኖሚ ዘረፍ ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ። ኤጀንሲው በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በከተማና በገጠር መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙትን የህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ኤጀንሲው የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ አባል መሆን የሚችሉ ዜጎች የአባልነትና ዓመታዊ መዋጮ በመክፈል እንዲመዘገቡ በመግለጽ ጥሪ አቅርቧል። የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚዛን ኪሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የ2012 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የአባላት ምዝገባና እድሳት መርሃ ግብር ከታህሳስ ወር ጀምሮ ይካሄዳል። በዚህም የጤና መድህን አባላት የሆኑ ሰዎችን የአባልነት እድሳት እንዲሁም አዳዲስ አባላትን ወደ ጤና መድህን የማስገባት ስራ ኤጀንሲው አገልግሎት እየሰጠባቸው ባሉት ክልሎች በመከናወን ላይ እንምደሚገኝ ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ ወደ ጤና ተቋማት ከሚሄዱ ህሙማን ውስጥ ሁለት በመቶ የሚሆኑት የጤና ወጪ ማውጣት አይችሉም። ይህንን ችግር ለመፍታት በመደጋገፍ መርህ ላይ የተመሰረተው የማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን መፍትሄ የሚሰጥ በመሆኑ ዜጎች የጤና መድህን አባል እንዲሆኑ ገልጸዋል። በመሆኑም በአንድ ሰው ወጪ መሸፈን የማይቻለውን የጤና ሽፋን ለማግኘት የሚመለከተው የህብረተሰብ ክፍል በዝቅተኛ መዋጮ የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው አንስተዋል። የጤና መድህን አገልግሎት በአምስት ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 657 ወረዳዎች ተጀምሮ በ509 ወረዳዎች አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። በጤና መድህን ስርዓቱ ከታቀፉት ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና አመታዊ የጤና መድህን መዋጮአቸውን መክፈል የማይችሉ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መዋጮው በመንግስት እዲሸፈንላቸው መደረጉንም አንስተዋል። በ2011 በጀት አመት ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የአባላት መዋጮ ከ1 ነጥን 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ጠቁመው፤ የጤና መድህን አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና መድህን ላገኙት የህክምና አገልግሎት ከ617 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል። የጤና መድህን ሽፋኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ፣ ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች ክልሎችና ከተሞች የጤና መድህን ሽፋኑን ለማስፋት እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።