የትግራይ ክልል ስርዓት ባልተከተለ የግብር አሰባሰብና የጉምሩክ አሰራር ምክንያት 450 ሚለዮን ብር አሳጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ስርዓት ባልተከተለ የግብር አሰባሰብና የጉምሩክ አሰራር ምክንያት 450 ሚለዮን ብር አሳጥቶታል
በግብር አሰባሰብና ጉምሩክ አስተዳደር በሚታየው የህግ ጥሰት ምክንያት የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ዓመት ብቻ ማግኘት የነበረበትን ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳሳጣው ተገለፀ፡፡ በንግድ ስርዓት ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የትግራይ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እንዳሉት፣ በንግድ እንቅስቃሴና በጉምሩክ አስተዳደር ላይ በርካታ ችግሮች ይታያሉ። ''በንግድ ግብር ላይ ፍትሃዊነት የጎደለው ህገ ወጥ አሰራርና የህግ ጥሰት ችግሮች በስፋት ይታይባቸዋል ያሉት የቢሮው ኃላፊ፣ በችግሮቹ ምክንያት የክልሉ መንግስት ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ማግኘት የነበረበትን ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አሳጥቶታል'' ብለዋል። በክልሉ ከ180 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ይገኛሉ ያሉት ዶክተር አብርሃም፣ ነጋዴዎቹ ከንግድ ከሚያገኙት ትርፍ የሚሰበሰበው የግብር ገቢ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ችግሩን እንዲስተካከል የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ግልፅነት ያለው አሰራር በማስፈን በተለይ ተጨማሪ እሴት ታክስን የሚያጭበረብሩ ነጋዴዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ ‘’በተጨማሪ እሴት ታክስ ዙሪያ የሚታየውን ማጭበርበር ለማስተካከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብር አሰባሰብ ስርዓት እየተዘረጋ ነው ‘’ ያሉት ደግሞ የፌደራል ገቢዎች ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ምህረት መናስብ ናቸው። ‘’ስነምግባር የጎደላቸው እና ብቃት የሌላቸው ሰራተኞች መበራከት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ናቸው’’ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ችግር በሚታይባቸው ሰራተኞች ላይ እርምጃ በመውሰድና ጥብቅ የታክስ ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2012 በጀት ዓመት 248 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬከተር ወይዘሮ አሰፉ ሊላይ በበኩላቸው በግብር ስርዓት ላይ የሚታየውን ህገወጥ አሰራር ለማስቀረት እና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል በዚህ ዓመት ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በመቀሌ ከተማ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ የተሰማሩ አቶ ፍፁም ለገሰ በሰጡት አስተያየት ''ግብር ለመክፈል በግለሰቦች በጎፈቃድ የተተመነ እንጂ በትክክለኛ መረጃ የተረጋገጠ እና ገቢን ያገናዘበ ስርዓት ባለመኖሩ ከራሴ ጀምሮ የሚገባኝን ዓመታዊ ግብር ለመንግስት ከፍያለሁ ብዬ አላምንም'' ብለዋል። ‘’አብዛኛዎቹ የትግራይ ክልል ነጋዴዎች ቫት ተመዘጋቢዎች ቢሆንም የሚደረገው ቁጥጥር የላላ በመሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች አየር በአየር በመሸጥ ህግ ተከትለን የምንሰራ ነጋዴዎችን ለኪሳራ እየዳረጉን ነው’’ ያሉት ደግሞ በመቀሌ በብረታ ብረት ንግድ ላይ የተሰማሩ አቶ አለም ገብረ ናቸው። በመሆኑም የሚመለከተው አካል በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ‘’የንግድ ፈቃድና መለያ ቁጥር ሳይኖራቸው የሚሰሩ ነጋዴዎች ህገወጥ ንግድ እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆኑ ምጣታቸውን’’የተናገሩት ደግሞ በዕጣን ንግድ የተሰማሩት አቶ ግርማይ እሸቴ ናቸው። የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የትግራይ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ እና የትግራይ ገቢዎች ልማት ባለስልጣን በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡