ቀጥታ፡

በምስራቅ አማራ የአምበጣ መንጋ ሶስት ሺህ 984 ሄክታር መሬት የለማ የማሽላ ሰብል ማውደሙ በጥናት ተረጋገጠ

ኢዜአ ታህሳስ 14/2012 በምስራቅ አማራ የአምበጣ መንጋ ሶስት ሺህ 984 ሄክታር መሬት ላይ ለምቶ የነበረ የማሽላ ሰብል እንዳወደመ በጥናት መረጋገጡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በዚህም  ምክንያት አርሶ አደሮች ከ102 ሺህ ኩንታል በላይ የሚገመት ምርት ማጣታቸው ታውቋል። በቢሮው የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን ለኢዜአ እንዳሉት የአንበጣ መንጋው ከመስከረም መጨረሻ ጀምሮ በምስራቅ አማራ በአምስት ዞኖች በሚገኙ 16 ወረዳዎች ተከስቶ ነበር። በወረዳዎቹ 155 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ ተከስቶ ከዚህ ውስጥ በሶስት ሺህ 984 ሄክታር የለማ የማሽላ ሰብል ማውደሙን ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ባደረገው ጥናት ማጋገጡን ገልጸዋል። በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ እንዲሁም በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በአውሮፕላንና የሰው ኃይል በተካሄደው ርጭት ከአምስት ሺህ ሊትር በላይ ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል። ቀሪው በሰብል የለማውና በአንበጣ መንጋው ተወሮ የነበረው መሬት ህብረተሰቡ ባደረገው የተቀናጀ የመከላከል ስራ እስከ ህዳር መጨረሻ የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን ባለሙያው አስታውቀዋል። በጥናቱ መሰረት በአንበጣ መንጋው ሰብላቸው የወደመባቸው ከ21 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችም ከ102 ሺህ ኩንታል በላይ የሚገመት ምርት በማጣታቸው በቀጣይ ድጋፍ የሚያገኘዩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የአንበጣ መንጋውን የጠፋ ቢሆንም አሁንም ድንገት ተደስቶ ጉዳት እንዳያደርስ የተጠናከረ የአሰሳ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝም አቶ አሻግሬ አመልክተዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ግርማ በበኩላቸው በዞኑ ቃሉ፣ ወረባቦ፣ አርጎባና ተሁለደሬ ወረዳዎች በአንበጣ መንጋው ከ30 ሺህ ሄክታር በላይ የሰብልና የግጦሽ መሬት ተወሮ እንደነበር ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም አንድ ሺህ 881 ሄክታር መሬት ላይ ለምቶ የነበረ የማሽላ ሰብል የወደመባቸውን አርሶ አደሮች በመለየት በሴፍትኔት ፕሮግራም ታቅፈው እርዳታ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከጥረቱ ውስጥም በዞኑ ከሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተወያይተው በደረሱት ስምምነት መሰረት ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች የቦሎቄ፣ ሽንብራና ማሾ ዘር ለማቅረብ በግዥ ሂደት ላይ የሚገኘው ተጠቅሷል። የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት ባደረሰባቸው በባቲና ደዋሀረዋ ወረዳዎች ከ685 ሄክታር በላይ መሬት የለማ የማሽላ ሰብል ማውደሙን የተናገሩት ደግሞ በኦሮሞ ብረሰብ አስተዳደርዞን ግብርና መምሪያ የስብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ገለቱ ናቸው። ኃላፊው እንዳሉት የማሽላ ሰብላቸው የወደመባቸውን ሶስት ሺህ 250 አርሶ አደሮችን የምግብ እህልና የዘር ድጋፍ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰሩ ናቸው። የአንጣ መንጋው በተከሰተባቸው በ16 ወረዳዎች አርሶ አደሮችን ጨምሮ ከ173 ሺህ በላይ የከተማ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎችና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመከላከል ስራ መሳተፋቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም