በክልል የመደራጀት ጥያቄዎቹ የህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት መሆናቸው ተረጋግጦ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በክልል የመደራጀት ጥያቄዎቹ የህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት መሆናቸው ተረጋግጦ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል - ምሁራን
ኢዜአ፤ ታህሳስ 14/2012 በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተነሱ ያሉ በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች የህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት መሆናቸው ተረጋግጠው ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግና የፌዴራሊዝም ምሁራን እንዳሉት የአገሪቷ ህገ-መንግስት ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በክልል የመደራጀት መብት ሰጥቷቸዋል።
በመሆኑም ''በክልል እንደራጅ'' የሚሉ ጥያቄዎች ሲነሱ ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው የሚል አስተያየት አላቸው።
በኢትዮጵያ በቅርቡ በህዝበ ውሳኔ ምላሽ ያገኘውን የሲዳማ ክልል ጨምሮ 10 ክልሎች አሉ።
የህግና የፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ ጥጋቡ በአገሪቷ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በማንነትና በክልል የመደራጀት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘታቸው ለግጭት መንስኤ ሲሆኑ እንደነበርም ገልጸዋል።
''በህገ-መንግስቱ በግልጽ የተቀመጠን የዜጎች መብት ማፈን ደግሞ አደገኛ ውጤት አለው'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ለገሰ፤ የእነዚህና መሰል ጥያቄዎች የህዝቡ ትክክለኛ ፍላጎት መሆናቸውን በማረጋገጥ ምላሽ መስጠት እነደሚገባ ነው ያነሱት።
የአመራር ጥበብ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አሰፋ በየነና የፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ሃይለየሱስ ታዬ ደግሞ በኢትዮጵያ አሁን ካለው ክልል ተጨማሪ ክልሎች ቢደራጁ የሚፈጠር ችግር እንደማይኖር ይስማማሉ።
በክልል መደራጀት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በፍጥነትና በቅርበት ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
ምንም እንኳን አገሪቷ ያላት ሃብት ውስን ቢሆንም ጥያቄው ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት የተነሳ ከሆነ ህዝቡን በተደጋጋሚ በማወያየት በህጋዊ መንገድ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በክልል ለመደራጀት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታና የዓለም ዓቀፍ ተሞክሮን ከግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ መሆኑንም አልሸሸጉም።
በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 39 ላይ "ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው" ይላል።
''ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ" ማለት ደግሞ "ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው፣ ሊግባቡት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው" በማለት ይበይናል።