አሜሪካ አነፍናፊ ውሾችን ወደ ጆርዳንና ግብጽ መላክ ልታቆም መወሰኗን አስታወቀች

145
ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም አሜሪካ ፈንጅ አነፍናፊ ውሾችን ወደ ጆርዳንና ግብጽ ላለመላክ ወስናለች ያለው ቢቢሲ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ሃገራቱ ባሳዩት ቸልተኝነት የተነሳ በርካታ ውሾች ከሞቱ በኋላ ነው  ተብሏል። በመስከረም ወር የወጣ አንድ የሃገሪቱ ሪፖርት ይፋ እንዳደረገው ከሆነም በጆርዳን፣ ግብጽና ሌሎች ስምንት ሀገራት ለግዳጅ ከተላኩ ከ100 በላይ ፈንጂ አነፍናፊ ውሾች በቸልኝነትና እንክብካቤ ጉድለት መጎሳቆላቸውን አሳይቷል። የአሜሪካ አነፍናፊ ውሾች የፀረ-ሽብር ፕሮግራሙን ለመደገፍ የተሰማሩ ሲሆን ጆርዳንም ሆነች ግብፅ በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ዓይነት አስተያየት አለመስጠታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ አሜሪካ ጊዜያዊ እገዳዋን ይፋ ባደረገችበት ወቅትም የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት እርምጃው የተወሰደው ተጨማሪ የፈንጅ አነፍናፊ ውሾችን ሞት ለመከላከል እንደሆነም ገልጿል። ባለስልጣን መስሪያቤቱ በማከልም አነፍናፊ ውሾቹ  ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረገውን የፀረ-ሽብር ተግባር ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪም የአሜሪካውያንን ሕይወት በመታደግ ቁልፍ ሚና እይተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸው፤ እ.ኤ.አ. በ2017 የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያወጣው ሪፖርት አንድ ውሻ በሃገረ ጆርዳን በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ህይወቱ አልፏል ብሏል። የአሜሪካ ባለሰልጣናትን ገለፃ ዋቢ ያደረገው ዘገባው እነዚያው አነፍናፊ ውሾቹ ተጎሳቁለውና ክብደታቸውም ስለቀነሰ ጤንነታቸው እስኪመለስና እስኪያገግሙ ድረስ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል ብሏል። በቅርቡ የወጣ ሌላኛ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ ወደ ጆርዳን ከተላኩ ውሾች ሁለቱ ተፈጥሮዓዊ ባልሆነ ምክንያት መሞታቸውን ዘገባው ጠቁማል። የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነም አንዱ ውሻ በከፍተኛ ሙቀት ሌላኛው ደግሞ አንድ የፖሊስ አባል በውሻው ላይ በረጨው የተባይ ማጥፋያ ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል፡፡ በርካታ አነፍናፊ ውሾች ከአሜሪካ ወደ ጆርዳን የሚሄዱ ሲሆን 100 ያህሉ ደግሞ በመከከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተሰማርተው እንደሚገኙም ተነግሯል። የአሜሪካ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነም ወደ ግብፅ ለግዳጅ ከተላኩ ውሾች አስር ያህሉ በሳንባ ካንሰር፣ በከፍተኛ ሙቀት እንዲሁም በተቀደደ የሽንት ፊኛ ምክንያት ተልእኳቸውን መፈፀም እንዳልቻሉ ቢቢሲ በዘገባው  አትቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም