ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የሚችል የስንዴ ልማት ተግባራዊ እያደረገች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የሚችል የስንዴ ልማት ተግባራዊ እያደረገች ነው
ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የሚችል የስንዴ ልማት ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊየን በላይ አምራቾች፤ ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት በዓመት እስከ አራት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ያመርታሉ። አገሪቷ በ 12 ተፋሰሶቿ አካባቢ ከአራት ሚሊየን ሄክታር በላይ ለእርሻው ምቹ የሆነ መሬት አላት። ከዚህ ውስጥ በ 500 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ብታለማ አሁን ባለው አማካይ የምርት መጠን 20 ሚሊየን ኩንታል ማግኘት ትችላለች። አሁን ያለው የስንዴ አቅርቦት ደግሞ 75 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፈን ቢሆንም የህዝቡ ፍላጎት ካለው አቅርቦት በላይ እያሻቀበ ነው። የግብርና ሚኒስቴር አቶ ዑመር ሁሴን እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በዚህም በተያዘው የበጋ መስኖ ልማት መርሃ ግብር 14 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ስንዴን በመስኖ ለማልማት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። የስንዴ ምርትን ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ኅብረተሰቡ በበጋ በመስኖ እንዲያመርት ግንዛቤ ፈጥረናልም ብለዋል። በሀገሪቷ ያለውን የስንዴ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመቀነስም በሶስት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የዘር ስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጿል። በኢትዮጵያ እስካሁን ለአፈሩ አይነት በትክክል የሚስማማ የስንዴ ምርጥ ዘር ማግኘት ባለመቻሉም ተቀራራቢ ዘር ሲጠቀሙ እንደነበር ገልጸዋል። በቀጣይ ግን ከምርምር ተቋማት ጋር በመተባበርና ሰፊ ጥናት በማድረግ ለአካባቢው የሚስማማ ምርጥ ዘር በአካባቢው እንዲመረት እናደርጋለን ብለዋል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በቅድሚያ ምርጥ ዘር መኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ የምርጥ ዘር ዝግጅት ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለምም ብለዋል።