ቀጥታ፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ከሱዳን መንግስት መሪዎች ጋር ተወያዩ

ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 ዓ.ም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ የተወያዩት ከሱዳን ሉኣላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀነራል ፋታህ አልቡረሃን እና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላህ ሀምዶክ ጋር ነው። ውይይቱ ያተኮረው በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት መንገድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ አስታውቋል።

ዶክተር ስለሺ በዚሁ ወቅት ለሌተናል ጀነራል ፋታህ አልቡረሃን እና ለዶክተር አብደላህ ሀምዶክ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተላከ መልዕክትም አድርሰዋል።

ውይይቱ የተካሄደው የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ሚኒስትሮች በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ሌሎች አተገባበሮች ላይ ያተኮረውና በካርቱም የተካሄደው የሶስትዮሽ ስብሰባ ጎን ነው።

በውይይቱ ላይ የአለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ባለው ግዙፉ የሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የሶስቱ አገራት ባለስልጣናት በግድቡ የቴክኒክ አፈፃፀምና አተገባበር ላይ ሲመክሩ ይህ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፣ የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በቅርቡ በዋሽንግተን ካካሄዱት ወይይት በኋላ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው።

የሶስቱ ሃገራት ሚንስትሮች በዚሁ መግለጫቸው በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሁሉንም ፍላጎት በሚያረካ መልኩ በትብብር እና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት አቋማቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም