በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሐረሪ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሐረሪ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አወገዘ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 13/2012 ዓ.ም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እንደሚያወግዝ የሐረሪ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ።
የጉባኤው አባላት በእምነት ተቋማት ላይ በተፈጸመው ድርጊት ማዘናቸውንም ገልጸዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ በእምነት ተቋማቱ ላይ በተደረገው ጥቃት ቤተክርስቲያን ማዘኗንና ተግባሩንም ማውገዟን ተናግረዋል።
የእምነት ተቋማትን በማቃጠልና ህብረተሰቡን በማጋጨት የራስን ፍላጎት ለማሳካት መሞከር ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ በዚህ ተግባር የተሰማሩ አካላት ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ መክረዋል።
"መንግስትም ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ለህግ በማቅረብ የፍርድ ውጤቱን ለህዝብ በግልጽ ማሳወቅ ይኖርበታል" ብለዋል።
"ድርጊቱ በየትኛውም የእምነት ተቋም ተቀባይነት የሌለውና የትኛውንም ሃይማኖት የማይወክል ተግባር ነው" ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ሼህ መሐመድ አሚን ናቸው።
እርስ በርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት ኢትዮዽያ የዓለም ተምሳሌት መሆኗን ያስታወሱት ሼህ መሐመድ ሕብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።
"አገርን በማረጋጋት ተግባርም የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል" ብለዋል።
የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ መጋቤ መስፍን በየነ በበኩላቸው በሞጣ ከተማ በእምነት ተቋማት ላይ በተፈጸመው ድርጊት ማዘናቸውንና ተግባሩንም ቤተክርስቲያኗ እንደምታወግዝ ተናግረዋል።
"ከፈጣሪ ጋር የሚያገናኘውን ቤተ እምነት ማቃጠልና ማውደም ሃጥያትም ወንጀልም ነው" ብለዋል።
ድርጊቱ አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመው በድርጊቱ የተሳተፉትን ተከታትሎ የመያዝና ለፍርድ ለማቅረብ መንግስት የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡም በሰላም፣ በትዕግስትና በማስተዋል በመንቀሳቀስ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባና በእኩይ ተግባር የሚሳተፉ አካላት ሲያጋጥሙትም ለመንግስት መጠቆም እንዳለበት ተናግረዋል።
"ድርጊቱ ኢሰብዓዊና ጉዳቱም ሁሉንም የሃይማኖት ተከታዮች ያሳዘነ ነው" ያሉት ሌላው የጉባኤው አቶ ዮሴፍ ፓውሎስ በበኩላቸው፣ በተለይ መንግስት አገራዊ ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ ባለበት ወቅት መፈጸሙ አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተባባሪ አቶ አበበ አራርሳ በበኩላቸው "መንግስት ጥቃቱን ባደረሱ አካላት ላይ አስተማሪና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት፤ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራን በተሻለ መፈጸምም ይኖርበታል" ብለዋል።
የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔውም ጉዳት የደረሰባቸውን የእምነት ተቋማት ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ በሚደረገው ድጋፍ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።