የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕብረተሰቡን ደህንነት ለማወክ የሚፈልጉትን አስጠነቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሕብረተሰቡን ደህንነት ለማወክ የሚፈልጉትን አስጠነቀቀ
ኢዜአ ታህሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም በግለሰቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን የብሔር መልክ በማስያዝ የህብረተሰቡን ደህንነት ለማወክ የሚጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስጠነቀቀ፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር መሀመድ ሃመደኒል ለኢዜአ እንደገለጹት ባፈው ሳምንት በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ አይፓፑ ቀበሌ በግለሰቦች መካከልተከስቶ በነበረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
ከድርጊቱ ጋር የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደቀደመ ሠላም መመለሱን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና የግለሰቦችን ግጭት የብሔር መልክ ለማስያዝ አንዳንድ የመንግስት የብዙሀን መገናኛዎችን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻው መቀጠሉን ኮሚሽነር መሃመድ አመልክተዋል፡፡
በግለሰቦች መካከል በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊከሰት እንደሚችል የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ "ከግጭቱ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት የክልሉ መንግስት አይታገስም፤ ይህን የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል" ብለዋል፡፡
በግጭቱ ላይ ከሚደረግ ምርመራ በተጨማሪ ጉዳዩን የሚያራግቡ አካላትን በህግ ለመጠየቅ የሚያግዙ ምርመራዎች እየተካሄዱ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሌላ ዜና በትናንትናው እለት ከአሶሳ ወደ ግልገልበለስ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አገር ቋራጭ አውቶብስ ላይ በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ያሬንጃ ቀበሌ አካባቢ ተኩስ በመክፈት ጉዳት ለማድረስ የሞከረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው በአውቶቡሱ ተሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ አንድ የክልሉ ልዩ ኃይል አባል ባደረገው የተኩስ ለውውጥ በጥይት ተመቶ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደኮሚሽነሩ ገለጻ በአውቶቡስ ውስጥ በነበሩ ተሳፋሪዎች ላይ ምንም የደረሰ ጉዳት የለም፡፡
ሕብረተሰቡም ለጸጥታ አስከባሪ አካላት የሚያደርገውን የተለመደ ትብብር እንዲያጠናክር ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
-