የድሬዳዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ የደረሰውን ጥፋት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ የደረሰውን ጥፋት አወገዘ
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012 የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ በኃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰን ጥፋት አወገዘ። የጉባኤው ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሞጣ ከተማ የደረሰው ጥፋት ሊሰማና ሊፈፀም የማገይባ እኩይ ተግባርን እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል፡፡ "ድርጊቱን በፅኑ እናወግዛለን፤ መንግስት አጥፊዎችን በፍጥነት ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነት ሊያረጋግጥ ይገባል"ብለዋል፡፡ ለሀገርና ለወገን ፀሎት የሚደረግባቸውን የእምነት ተቋማትን ማቃጠልና ማውደም እጅግ አስጠያፊና የሚወገዝ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ተወካይ ሼህ መሐመድ አብደላ ናቸው። ድርጊቱ በመንፈሳዊም ሆነ በምድራዊ ህግ የሚያስጠይቅና የህዝብን ቁጣ የሚቀሰቅስ ተግባር ቢሆንም ድርጊቱ በፍቅርና በህብረት ዘመናት የተሻገሩትን ህዝቦች አብሮ የመኖር ጉዞን እንደማያሰናክለው አስታውቀዋል። " እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ እኩይና የሚወገዝ ተግባር ነው በየትኛውም ኃይማኖት ተቀባይነት የለውም"ብለዋል፡፡ የወደሙት ቤተ-እምነቶች ዳግም በዚያው ስፍራ ተተክለው ምዕመናኑ የቀድሞ ኃይማኖታዊ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ መረባረብ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ የድሬዳዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ መጋቢ ሚኪያስ ታዬ በበኩላቸው "ፍቅርና ህብረታችን አጠናክረን የኢትዮጵያ የሰላምና የፍቅር አምባነት በጋራ ልንጠብቅ ይገባል" ብለዋል፡፡ አማኙን ህብረተሰብ ለማጋጨት በሞጣ ከተማ የተፈጸመው እኩይ ተግባር እንደሚያወግዙም አስታውቀዋል። ድርጊቱ ኢትዮጵያችን በአለም አደባባይ እየገነነችና ታላቅ ስሟን ዳግም እየገነባች ያለችበት ሂደት ያልተዋጠላቸው አካላት የፈፀሙት አሳዛኝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "በሞጣ አካባቢ ያሉ ወንድሞቻችን ፣እህቶቻችን መንግስት አንድ መፍትሄ እስኪሰጥ ድረስ ተረጋግተው የተለመደ ኃይማኖታዊ ተግባራቸውን እንዲያከናው ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል፡፡ በተለይም ወጣቱ ወደሚያምንበት ቤተ-እምነት በመምጣት ለሰላምና ፍቅር ቦታ እንዲሰጥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡