ቀጥታ፡

የጎሬ- ማሻ- ቴፒ 142 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 ዓ.ም የጎሬ- ማሻ- ቴፒ 142 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የመንገዱ ግንባታ የፌደራልና የየክልሎቹ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት በይፋ ተጀምሯል።

ግንባታው በ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወነው ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት እና ከደቡብ ኮርያው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የሚሸፈን ነው።

አቶ ሳምሶን እንዳሉት የመንገዱ ግንባታ ሥራ በደቡብ ኮርያው "ሀዩንዳይ ዴቬሎፕመንት ካምፓኒ" የሚከናወን ሲሆን በአራት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

የቁጥጥር እና የማማከር ስራውንም የኮርያው "ሱሶንግ ኢንጂነሪንግ" እና አገር በቀሉ "ኔት ኮንሰልቲንግ" በጋራ እንደሚያከናውኑት አቶ ሳምሶን ገልጸዋል።

አቶ ሳምሶን እንዳሉት የኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ጋምቤላ ክልሎችን የሚያስተሳስረው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን የቡና፣ ማር እና ቅመማ ቅመም ምርቶችን በተቀላጠፈ መልኩ ለገበያ ለማቅረብ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ህብረተሰቡና የመንግስት አካላት ካሳ የተከፈለባቸውን ንብረቶች በፍጥነት በማንሳት እንዲተባበሩም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል::

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የመንገድ ዘርፍ ልማቱ ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን በሚደግፍ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 90 የሚደርሱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የጨረታ ሂደት በማጠናቀቅ ወደሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው የጎሬ-ማሻ-ቴፒ የጠጠር መንገድ ግንባታ መጀመር የሦስቱን ክልሎች የጋራ ልማት እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ ተጠናቆ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት

እንዲያግዝ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም