ቀጥታ፡

ከብልጽግና ፓርቲ ምን ይጠበቃል?

ኢዜአ ታህሳስ 12 / 2012  ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) አባልና አጋር ፓርቲዎች ውህደት ከተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ ቀዳሚ ተግባራት ምን መሆን አለባቸው? በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ሁኔታና የኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ሽግግርን አስመልክቶ ምሁራንን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ብልጽግና ፓርቲ ባነገባቸው አስተሳሰቦች መካከል ለአሁኑ አገራዊ ሁኔታ ቅድሚያ መስጠት ስላለባቸው ጉዳዮች በተለይም ለኢዜአ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ መስዑድ ገበየሁ ወደ ውህደት የመጣው ፓርቲ ሰብዓዊነት፣ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ብዝሃነት አስተሳስብ ማካተቱ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ተገቢነት እንዳለው ያምናሉ።

በመርህ ደረጃ ቢስማሙም ግን ከኢህአዴግ ዘመንም ሆነ ከዛ በፊት የዜጎች ክብርና መብቶች ሲከበሩ እንዳልነበረ ገልጸው፤ ''ፓርቲው በተግባር ከተለወጠ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ሚዲያ ነጻነት ላይ ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል'' ይላሉ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ1960ና 1970ዎቹ ጀምሮ የተዛባ አካሄድ እንደነበረው የሚናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ታደሰ ጃለታ ናቸው።

በነበረው ስርዓት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት ሳይሆን ክልሎች ሌላ ስሜት፣ ታሪክ እየፈጠሩ ወደ ኮንፌዴሬሽን ስቴት እሳቤ እንዲሄዱና አገር እንድትበታተን ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራሊዝም ትግበራው ፍትሃዊ ያልነበረ፣ ይልቁንስ እንደ ስርወ መንግስት በአንድ አካባቢ የፖለቲካ ልሂቃንና ከነርሱ ጋር በተሳሰሩ ግለሰቦች የሚዘወር ኢኮኖሚያዊ ስርዓት እንደነበር ገልጸዋል።

የዶክተር ታደሰን ሃሳብ የሚጋሩት የራያ ማምነት ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ደሳለኝ ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግስት ስር ሳለች መቀንቀን የጀመረው የብሔር ጥያቄ በኢህአዴግ ዘመንም ትክክለኛ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል ይላሉ።

የብሔር ጥያቄ ግቡ በእኩልነት መኖር ቢሆንም ላለፉት 27 ዓመታት ሲሰራበት የቆየው ግን ብሔሮች እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ፣ አንድ ከሚያደርጋቸው ይልቅ የሚለያያቸው ላይ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው፤ ፓርቲው የመጣበትን መንገድ ማረምና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ ፓርቲና መንግስት የተለያዩ በመሆናቸው የኢህአዴግ ወደ ውህደት መምጣቱ ፌዴራሊዝምን የሚቃረን ወይም አሃዳዊነትን የሚያመጣ እንዳልሆነ አብራርተዋል።

ውህደቱን ያልተቀላቀለውና በብቸኝነት የተቃወመው የኢህአዴግ አባል ድርጅት ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የተቃውሞው ምንጭ የበላይነቱንና ጥቅሙን የሚያስቀር እንደሆነ ገልጸዋል።

ፓርቲው በትክክል ተለውጫለሁ ካለ በቅድሚያ ስህተቱን ማመን፣ በመቀጠልም ከብሔር ተኮርነት ወደ አገራዊ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ተናግረዋል።

ፓርቲው በተለይም ቅድሚያ መስጠት ያለበት በርካታ ችግሮች ያሉበትን ህገ መንግስትና ለዜጎች አብሮ የመኖር እሴትን የሚቃረኑ የክልል ህገ መንግስታት ማሻሻልና የስራ ቋንቋን መጨመር እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም