የኢትዮጵያ ባህል ቡድን የኤርትራ ቆይታ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ለሚሰሩ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባህል ቡድን የኤርትራ ቆይታ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ለሚሰሩ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው
ኢዜአ ታህሳስ 12/2012 የኢትዮጵያ ባህል ቡድን የኤርትራ ቆይታ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ለሚሰሩ ቀጣይ ስራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ የተመራው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን የማጠቃለያ ዝግጅቱን ትናንት ማምሻውን በአስመራ አድርጓል።
ቡድኑ ከ60 በላይ አባላት የያዘ ሲሆን በቆይታው ከአስመራ በተጨማሪ በከረንና ምጽዋ የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን አቅርቧል።
የባህል ቡድኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከተዋቂ ድምጻዊያንና ጃኖ ባንድ የተካተቱበት ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት የባህል ቡድኑ ጉዞና ቆይታ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን አላማ ያደረገ ነው።
በአገራቱ መካከል የሰፈነው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረውና የሁለቱ አገራት አጠቃላይ ግንኙነት ማጠናከርንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
በነበሩት የሙዚቃ ዝግጅቶች በየከተሞቹ ያለው ነዋሪ በየዝግጅቶቹ በመታደም ለባህል ቡድኑ ያለውን የደስታ ስሜት ሲገልጽ እንደነበርም ተናግረዋል።
የባህል ቡድኑ ቆይታ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና በቀጣይ ለሚሰሩ የዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስራዎችም ያለው ሚና የጎላ እንደሆነም ነው አቶ ነቢያት ያስረዱት።
ከሙዚቃ ዝግጅቱ በተጨማሪ የሁለቱን አገራት የዲፕሎማሲና ሌሎች ግንኙነቶችንም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
በቀጣይም የሁለቱን አገራት ህዝቦችና መንግስታት ግንኙነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ስራዎች በሚኒስቴሩ በኩል ይሰራሉ ብለዋል።
በህዳር 2012 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በዩጋንዳ የአምስት ቀናት ቆይታ አድርጎ ነበር።
በተጨማሪም የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በህዳር 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ቆይታ አድርጎ እንደነበረም የሚታወስ ነው።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑት የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ስራዎች ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ነው አቶ ነቢያት የገለጹት።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን ሚኒስቴሩ በያዘው እቅድ መሰረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ለአንድ ሳምንት ቆይታ ለማድረግ ወደ ኤርትራ ያቀናው የኢትዮጵያ የባህል ቡድን ነገ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
የባህል ቡድኑ ከሙዚቃ ዝግጅቶቹ በተጨማሪ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኤርትራ የባህል ቡድን ባለፈው የካቲት 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳርና በሀዋሳ ከተማዎች ማቅረቡ የሚታወስ ነው።