የባህል ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የባህል ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል
ኢዜአ ታህሳስ 13 / 2012 --- የኢትዮጵያ ባህል ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ። የትግራይ ክልል 14ኛው የባህል ስፖርት ውድድር በኮረም ከተማ ተካሂዷል። የዘርፉ ባለሙያዎችና ስፖርተኞች ለኢዜአ እንዳሉት፣ ዘመናዊ ስፖርት ከመምጣቱ በፊት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ሲዘወተር የነበረው የባህል ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። በትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንዳመኾኒ ወረዳ የባህላዊ ስፖርት አሰልጣኝ መምህር ዳርጉ አለሞ እንዳሉት፣በአገር አቀፍ ደረጃ ህግና ደንብ የወጣላቸው በርካታ የባህል ስፖርቶች አሉ። "ይሁንና የባህል ስፖርቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቁ የተደረጉ ጥረቶች በርካታ ክፍተት ያሉባቸው ናቸው" ብለዋል። ወጣቶች ከባህላዊ ስፖርት ይልቅ ዘመናዊ ስፖርት ላይ ማተኮራቸው ባህላዊ ስፖርቱን የዕድሜ ጠገብነቱን ያህል እንዳያድግ እንቅፋት እንደሆነበት አሰልጣኙ ተናግረዋል። በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ አዘቦ ወረዳን በመወከል በባህላዊ የትግል ስፖርት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በመሳተፍ ሰባት ሜዳሊያዎችን ያገኘው ስፖርተኛ ወጣት ታደለ ባርያ በበኩሉ፣ ለባህላዊ ስፖርት የሚሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢሻሻልም አሁንም ብዙ መስራት እንደሚገባ ገልጿል። ከዚህ በፊት በባህል ስፖርት በቁጥርም ይሁን በጥራት ብዙ ተወዳዳሪ እንዳልነበረ የገለፀው ወጣት ታደለ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰነ መልኩ ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን እየወጡበት መሆኑን አመልክቷል። "ባህላዊ ስፖርቱ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሌሎች ዘመናዊ ስፖርቶች የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብሏል። በትግራይ ማዕከላዊ ዞን መረብለከ ወረዳን በመወከል ለመጀመሪያ ጊዜ በ"ቡብ" ባህላዊ ስፖርት እየተካፈለች የምትገኘው ወጣት ተወዳዳሪ ትርሀስ ተስፋይ በበኩሏዋ፣ ተከታታይ የሙያ ስልጠና ቢሰጥ በርካታ ስፖርተኞችን በዘርፉ ማፍራት እንደሚቻል ገልፃለች። "በክልላችን በባህላዊ ስፖርት የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችና ወረዳዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ መጥቷል’’ ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ባህላዊ ስፖርት ሥራ አስፈጻሚ መምህርት ለተብርሃን አበበ ናቸው። በ13ኛው የትግራይ ክልል ባህላዊ ስፖርት ውድድር ላይ 28 ወረዳዎችና 405 ተወዳዳሪዎችን ተሳትፈው እንደነበሩ አስታውሰው፣ ዘንድሮ በተካሄደው ውድድር ላይ ከ34 ወረዳዎች የተውጣጡ 550 ተወዳዳሪዎች እየተካፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። "ምንም እንኳን በክልል እና በአገር አቀፍ ደረጃ የባህል ስፖርት እያደገ ቢመጣም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ አንፃር ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል መምህርት ለተብርሃን። ባህላዊ ስፖርቱ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ታጥሮ እንዳይቀርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል ። "ህብረተሰቡ ስፖርቱን እያዘወተረ ሲመጣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ያግዛል" ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ፣ የሌሎች አገራት ስፖርተኞችን በመጋበዝ የማስተዋወቅ ሥራ ለመስራት ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል። በኮረም ከተማ ለዘጠኝ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 14ኛው የትግራይ ባህላዊ የስፖርት ውድድር ትናንት ተጠናቋል።