ቀጥታ፡

ባንኩ በአፋር ክልል ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፉን ከፈተ

ኢዜአ ታህሳስ 12/ 2012 ---የኢትዮጵ ንግድ ባንክ በአፋር ክልል የመጀመሪያው የሆነውን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፉን ከፈተ። "ሱልጣን አሊሚራህ" በሚል ስያሜ የተከፈተው የባንኩ ቅርንጫፍ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በተገኙበት  ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ-መሰተዳድር አቶ አወል አርባ እንዳሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የክልሉን ህብረተሰብ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልገሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረው እርምጃ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል ካማሳድግ በለፈ ለዘመናት ሲያነሳው ለነበረው ጥያቄ መልስ የሰጠ ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ባንኩ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በአግባቡ በመጠቀም የቁጠባ ባህሉን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል። በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ህብረተሰቡ ከባንኩ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጌና በበኩላቸው ባንኩ ከ1 ሺህ 520 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች ውስጥ በሚገኙ መስኮቶች ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። "በእነዚህ ቅርንጫፎቹ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል። አገልግሎቱን ከሚጠቀሙ ደንበኞች ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ በማሰባሰብ የሼሪአ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብር ብድር ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። አቶ በጫ እንዳሉት ባንኩ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የባንክ አገልግቶችን በማስፋፋት የክልሉ ንግድ እንቅስቃሴ እንዲፋጠን የጎላ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በክልሉ የመጀመሪያ የሆነውን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ "የሱልጣን ኢሊሚራህ" ቅርንጫፉን በይፋ አስመርቆ ሥራ መጀመሩን ነው የተናገሩት። "ባንኩ እየሰጣቸው ካሉ አገልግሎቶች መካከል የተቀማጭ ገንዘብና የኢንቨስትመንት፣ የብድር አገልግሎት ዋስትና መስጠት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ንግድ ድጋፍና የሃዋላ አግልሎቶች ይገኙበታል" ብለዋል። እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ ባንኩ ለአገርና ለህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባበረከቱ ታላላቅ ሰዎች ስም ቅርጫፎችን በመክፈት ትውልዱ ሁሌም እንዲያስታውሳቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። የሱልጣን አሊሚራህ ቅርንጫፍ ለእዚህ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል። የሱልጣን አሊሚራህ ቅርንጫፍ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት  በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። ቅርንጫፉ ከለወድ ነጻ አገልግሎት ከሚሰጡ የንግድ ባንክ ቅርጫፎች ውስጥ 31ኛ መሆኑን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም