ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ18 ዓመታት በፊት ተቋርጦ የነበረውን የአቴንስ በረራ አገልግሎት ጀመረ

ኢዜአ፤ ታህሳስ 12/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ18 ዓመታት በፊት ተቋርጦ የነበረውን የግሪክ አቴንስ በረራ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ።

አየር መንገዱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የግሪኳ አቴንስ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መረብ ውስጥ ተቀላቅላለች።

አየር መንገዱ ታህሳስ 8 ቀን 2012 ዓ.ም የጀመረው የአቴንስ በረራ በአለም ላይ በሁሉም አህጉራት ያሉትን መዳረሻዎች ወደ 127 ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

አየር መንገዱ እጅግ ዘመናዊና የአገልግሎት ዘመናቸው በአማካኝ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 125 አውሮፕላኖችን አገልግሎት ላይ ማዋሉን አስታውቋል።

በተለይ ባለፈው ዓመት ብቻ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ 10 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ተረክቦ ለአገልግሎት አሰማርቷል።

አየር መንገዱ በ2025 እድርስበታለሁ ብሎ  ያስቀመጠውን ራእይ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በአራት እጥፍ ማደጉ ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ መሪ ከመሆን ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

ከዚህ ባሻገርም በርካታ ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችንና ሽልማቶችን መቀበሉን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚሁ ሳምንትም ወደሂውስተን አሜሪካ አዲስ የበረራ አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም